ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው። @tikvahuniversity @tikvahethAfaanOromoo @tikvahethmagazine @tikvahethsport @tikvahethiopiatigrigna #ኢትዮጵያ
በመዲናዋ የትንሣኤ በዓል እንዴት አለፈ ?
በ2017 ዓ/ም የትንሣዔ በዓል የተለያዩ ደንቦችን በተላለፉ አሽከርካሪዎች እርምጃ መወሰዱን፣ የበዓል ዋዜማ አንድ ሰው በመኪና አደጋ መሞቱን የአዲስ አበባ ከተማ ፓሊስ ኮሚሽን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጸ።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ምን አሉ ?
“ ከወንጀል አንጻር ስንመለከት፥ በመደበኛነት ከሚፈጸሙ እንደሌብነት፣ ጸብ፣ ቅሚያና የመሳሰሉ ከመጠጥ ጋር የተገናኙ ድርጊቶች ካልሆኑ በስተቀር ከበዓሉ ጋር በተገናኘ ከባድ ወንጀል የተፈጸመበት ጊዜ አልነበረም።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ኮድ 2 64942 አውቶብስ የ50 ዓመት እድሜ ያላቸው ሰው በውስጥ ለውስጥ መንገድ ወጥተው ሲሻገሩ ገጭቷቸው ህይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል።
የትራፊክ አደጋ ላይ በአልኮል መጠጥ ፍተሻ ጭምር ቁጥጥር አድርገናል። በዚህም በአልኮል ጥሰት ወደ 1,072 አሽከርካሪዎችን ተፈትሽዋል። 33 አሽከርከሪዎች ከመጠን በላይ ጠጥተው ሺያሽከረክሩ ተገኝተው በደንብ መተላለፍ ቅጣት ተወስዶባቸዋል።
ከመጠን በታች የጠጡ ደግሞ ወደ 41 አሽከርካሪዎች አግኝተናል። አልኮል ጠጥተዋል፤ ግን መጠኑ ከ0.4 በላይ አይደለም። ከፍተኛ የሚባለው ከዚህ በላይ ሲሆን ነው። ግን ይሄም አደጋ የሚያደርስ ስለሆነ አስተምረን ለቀናቸዋል።
ሌሎች ልዩ ልዩ ደንቦችን የጣሱ አሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር አድርገናል። ወደ 99 አሽከርካሪዎች ደንብ ሲተላለፉ ተገኝተው አስፈላጊው እርምጃ ተወስዶባቸዋል። በዓሉ በጣም ደማቅ ነበር፤ ከድምቀቱና ከሰው ብዛቱ አንፃር ሰላማዊ በዓል አሳልፈናል ማለት ይቻላል ” ብለዋል።
ሰዎች ወንጀል ሲፈጽሙ ብዙ ጊዜ በጥቅል “እርምጃ ተወስዶባቸዋል” ነው የሚባለውና በሾፌሮቹ የተወሰደው እርምጃስ ምንድን ነው ? ስንል ላቀረብነው ጥያቄም፣ “ ከ70 በላይ ደንብ መተላለፎች ናቸው። 70ዎቹንም መጥቀስ አይቻልም ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በበዓሉ ህገ ወጥ የብር ኖት ማጭበርበር፣ በምግብና መጠጥ ላይ በዓድ ነገሮችን ቀላቅሎ ከመሸጥ አንፃር የተፈጸመ ወንጀል ካለ ስንጠይቃቸውም፣ እስካሁን የደረሳቸው የክስ ሁኔታ እንደሌለ፣ ካለ ግልጽ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።
ኮማንደር ባስተላለፉት መልዕክት ምን አሉ ?
“ ከዚህ በኋላም የሰርግ ወራት ነው፤ በተለይ የትራፊክ አደጋ ሥጋት አለብን ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። አልኮል ጠጥተው የሚያሽከረክሩ ሹፌሮች እንደሚበዙ ይገመታል።
አሽከርካሪዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሰው ስለሚበዛ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ ሰውና እቃን አንድ ላይ መጫን እና የመሳሰሉ ደንብ መተላለፎች ሊበዙ ይችላሉ ተብሎ ስለሚገመት ጥብቅ ቁጥጥር እናደርጋለን።
የትራንስፓርት መጠበቂያ፣ በጥቅሉ ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች የኪስ ቀበኞች ሊኖሩ ስለሚችሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ” ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
"በግል ጥረታችን ስራ አግኝተን ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ አስፈላጊውን ዶክመት ብናሟላም መንግስት ከሀገር እንዳንወጣ ከልክሎናል " - ሥራ አጥ ወጣቶች
ቁጥራቸው 30 የሚጠጉ ወጣቶች በኩዊት ሀገር በራሳቸው ጥረት ሥራ ፈልገው ለማግኘት እስከ 500 ሺ ብር ወጪ አድርገው በራሳቸው ጥረት ቢያገኙም ፈቃድ እንደተከለከሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቅሬታ አቅርበዋል።
በመጨረሻም ለጉዞ ያስፈልጋል የተባለውን QR ኮድ ለመጠየቅ ወደ ሰራተኛና ማህበራዊ ሚንስቴር ቢሄዱም ጉዞው ታግዷል ተብለናል ብለዋል።
QR ኮዱ አስላጊው ዶክመንቶች መሟላታቸውን አረጋግጦ በኦላይን ላይ ከተጫነ በኋላ የሚሰጥ ሲሆን ኤርፖርት ላይ ኢሚግሬሽን አስፈላጊውን ዶክመንት መያዛቸውን የሚያረጋግጥበት ነው። ይህንን አገልግሎት ለማግኘትም 20 ሺ ብር ክፍያ ይጠይቃል።
በጅማ ዩንቨርሲ ባለፈው ዓመት የማዕረግ ተመራቂ እንደነበረ እና ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ወጣት ላለፍት 8 ወራት በሀገር ውስጥ ስራ ለማግኘት ቢሯሯጥም ሥራ የማግኘት እድሉ ጠባብ እንደሆነበት ይናገራል።
በዚህም በኩዊት ሀገር የሚኖር ዘሙዱ ሥራ እንዳገኘለትና መንጃ ፈቃድ ያስፈልግ ስለነበረ እሱን ጨምሮ የጉዞ ዶክመንቶችን ለማሟላት ከ 500 ሺ ብር በላይ መጨረሱን ይገልጻል።
በመጨረሻም ከሰራተኛና ማህበራዊ ሚንስትር በኩል ያስፈልጋል የተባለ QR code ለማስደረግ ወደ ሚኒስቴሩ ቢሄድም እሱን ማድረግ እንደማይችል እንደተነገረው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።
ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር በተደጋጋሚ በመሄድ ምክንያቱን ለመጠየቅ ጥረት እንዳደረገና በመጨረሻም "ከበላይ አካል የመጣ ትዕዛዝ" ነው መባሉን መስማቱን ገልጿል።
ከአንድ ቀን በፊት ይሄን አገልግሎት ለማግኘት አብሮ ከሄደው ጓደኛው እሱ አንድ ማኅተም ይቀርኃል ተብሎ ሲመለስ ጓደኛው አገልግሎቱን ማግኘቱን፤ በቀጣዩ ቀን ግን "አገልግሎት መስጠት ታግዷል" መባሉን አስረድቷል።
እርሱና ሌሎች 30 የሚጠጉ ተመሳሳይ ችግር ያጋጠማቸው ወጣቶች ተሰባስበው ወደ ሥራና ክህሎት ሚንስቴር ቢሄዱም መልስ የሚሰጣቸው አካል እንዳላገኙ ተናግሯል።
በዚህ ሁኔታ ከአንድ ወር በላይ እየተጉላሉ እንዳሉ የሚናገረው ይህው ወጣት ቫዛቸውን ጨምሮ ጠቃሚ የሆኑ ዶክመንቶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው እየተቃጠለ እንደሆነ ገልጿል።
አብረዋቸው ሲጠይቁ ከነበሩት ውስጥ "አንዳንዶቹ ተስፋ በመቁረጥ በህገወጥ መንገድ በጀልባ ከሀገር እየወጡ ነው" ሲል ያስረዳል።
በተመሳሳይ ምክንያት ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ ወጣት በግል ጥረቱ ወደ ኩዊት ለመሄድ አስፈላጊ ለሚባሉ ዶክመንቶችም ግማሽ ሚልየን ብር የሚሆን ወጭ ማውጣቱን ገልጾልናል።
በመጨረሻም QR ኮዱን ለማግኘት ወደ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ስሄድ ጉዞው ታግዷል መባሉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።
ጉዳዩ ይመለከተዋል ወደ ተባለው ጉዞው እንዲታገድ አቅጣጫ ሰጥቷል ወደተባለው የስራና ክህሎት ሚንስቴር ቲክቫህ ኢትዮጵያ ደውሎ ነበር።
በህዝብ ግንኙነት ሰራተኞች በኩል መልስ ለሚሰጠው አካል ጥያቄ ቀርቦ ከዛም ጥያቄው ማን መመለስ እንዳለበት ሰው ይመደባል በተባልነው መሰረት ጥያቄውን በጹሁፍ ብናቀርብም ከሚኒስቴሩ በኩል ምላሽ ማግኘት አልተቻለንም።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ በሚኒስቴሩ በኩል ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
#EOTC
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪ በሆኑት በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ፍራንሲስ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ለመላው የሮማ ካቶሊካዊ መሪዎች እና በመላው ዓለም ላሉ ምእመናን እንዲሁም በኢትዮጵያ ላሉ ካቶሊካውያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስም ገልጸዋል።
@tikvahethiopia
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሀዘን መግለጫ ፦
" የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ዛሬ በሰማነው እጅግ አሳዛኝ ዜና የብጹዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ አለም ድካም ማረፍ የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን መላው ካቶሊካውያን እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ ለቅዱስ አባታችን ዘለዓለማዊ እረፍት በጸሎት አብራችሁ እንድትሆኑ ጥሪ እናቀርባለን።
ጌታ ሆይ ለሞቱት ሰዎች
የዘላለም እረፍት ስጣቸው
የዘላለም ብርሃን አብራላቸው
በሰላም አሳርፋቸው። "
@tikvahethiopia
" ህዝባችንን ከዚህ ኋላቀር ገዢ ሃይል ለማላቀቅ ሁሉንም ዓይነት ትግል እናካሂዳለን " - አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት የህወሓት ኃይል
አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት የህወሓት ኃይል " ሌሎችን ያገለለና አቃፊ ያልሆነ ካቢኔ ተቋቁሟል " በሚል ተቃውሞውን ገለጸ።
አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስታዳደር ካቢኔ ወደ ስራ መግባቱን ፕሬዚዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ አሳውቀዋል።
" የአንዱን ህገ-ወጥ ቡድን ፍላጎት ብቻ በማድመጥ ሌሎች ያገለለ አቃፊ ያልሆነ ካቢኔ ማቋቋም ተቀባይነት የለውም " ሲል በአቶ ጌታቸው የሚመራው የህወሓት ሃይል ተቃውሟል።
አዲሱ ካቢኔ በአስቸኳይ እንዲስተካከል ጠይቋል።
በይፋ ባሰራጨው መግለጫ " በባለፈው ጊዚያዊ አስተዳደር ላይ ወታደራዊ መፈንቅለ ስልጣን ተካሂደዋል " የሚል አገላለፅ ተጠቅሟል።
" በትግራይ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በማካሄድ ስልጣን ከተያዘ 40 ቀናት ተቆጠረዋል " ያለው ይኸው የህወሓት ኃይል " የአቶ ጌታቸው አስተዳደር ህገ-ወጥ ተግባሩ ተጋግሎ ወደ ተባባሰ ግጭት እንዳያመራ ስልጣን ጭምር ለሰላም ሲል አሳልፎ ሰጥቷል " በማለት ገልጿል።
" አዲሱ ፕሬዜዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ በፌደራል መንግስትና በዓለም አቀፍ ተቋማት ወኪሎች ፊት የፈረሙት ሰነድ ሳይውል ሳያድር በመጣስ ወደ አንድ ወገን ያደላ ካቢኔ አቋቁመዋል " በማለትም ተችቷል።
በተግባር ያልተደገፈ ነው ሲል የገለጸው " አሸናፊ እና ተሸናፊ የለም " የሚል ተደጋጋሚ ንግግራቸውን አብጠልጥሎታል።
የተጀመረው ለውጥ የሚስቀጥል እንጂ ወደ ኋላ የሚመልስ አካሄድ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጾ የተቋቋመው ካቢኔ በአስቸኳይ እንዲስተካከልና አቃፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል።
ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ህዝቡን " ኋላቀር ገዢ " ካለው ሃይል ለማላቀቅ ሁሉም ዓይነት ትግል እንደሚያካሂድ አስጠንቅቋል።
ይህንን አቋሙንም " የፌደራል መንግስትና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በግልፅ ይወቁልኝ " ብሏል።
የአዲሱ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ አዲሱ ካቢኒያቸው ወደ ስራ መግባቱ ይፋ ባደረጉበት ወቅት ለቀድሞ ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳና በኋላፊነት ለሌሉ ሌሎች የካቢኔ አባላት ምስጋናና እውቅና ለመስጠት ያለመ ስነ-ስርዓት ይካሄዳል ብለው ነበር።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መቐለ
@tikvahethiopia
#Ethiopia #Kenya
ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሞያሌ ድንበር የንግድ ልውውጥን በ1 ሺህ ዶላር ጣሪያ ለመጀመር ተስማሙ።
ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለሁለት ዓመታት በዘለቀ ድርድር በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ማዕቀፍ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥን ለማቀላጠፍ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በዚህም መሰረት በሞያሌ ድንበር ላይ ለሚደረጉ የሸቀጦች ንግድ የመጀመሪያ ጣሪያ 1 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንዲሆን ተወስኗል።
በሞምባሳ የተጠናቀቀው ይህ ስምምነት የንግድ ሂደቶችን በማቅለል የድንበር ማህበረሰቦችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ያለመ ነው።
በስምምነቱ የኢትዮጵያ የድንበር ንግድ ዞን ከሞያሌ በ50 ኪሎ ሜትር እንዲሁም የኬንያ ደግሞ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚወሰን ነው።
ነጋዴዎችም በጋራ በተስማሙበት የምርት ዝርዝር መሰረት እስከ 1 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ የንግድ ልውውጥ በወር እስከ አራት ጊዜ ድረስ ማካሄድ ይችላሉ ተብሏል።
ይህ ስምምነት የንግድ ዋጋ ጣሪያዎችን፣ የጉዞ ድግግሞሽን እና የድንበር ንግድ ዞኖችን የመሳሰሉ ጉዳዮችን በመዳሰስ ለሁለት ዓመታት በዘለቀ ድርድር የተገኘ ውጤት ነው ተብሏል።
መረጃው የካፒታል ጋዜጣ ነው።
@tikvahethiopia
#ትንሣኤ
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ !
" በዚህ የለም ፤ እርሱ እንደተናገረው ተነሥቷል "
በማቴዎስ ወንጌል ፥ " እነሆ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዶአልና ፤ ቀርቦም በመቃብሩ አፍ ላይ ድንጋይዋን አንከባሎ በላይዋ ተቀመጠ፡፡
መልኩም እንደ መብረቅ ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበር፡፡
እርሱንም ከመፍራት የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁ ታወኩ ፤ እንደ በድንም ሆኑ፡፡
መልአኩ መልሶ ሴቶቹን እንዲህ አላቸው፥ ' እናንተስ አትፍሩ ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና፡፡ በዚህ የለም ፤ እርሱ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል ' " ተብሎ እንደተጻፈው መድኃኒዓለም ብርሃንን ተጎናጽፎ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን በክብር ተነሥቶአል፡፡
መልካም የትንሣኤ በዓል !
በዓሉ የሰላምና የፍቅር ይሆን ዘንድ እንመኛለን !
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
#TikvahEthiopiaFamily
@tikvahethiopia
" በመስቀልና በትንሣኤው የተሰበረው ይጠገናል፤ የደከመው ይበረታል፤ የወደቀው ይነሣል፤ የተሸነፈው ያሸንፋል ይህንንም ለማክበር በትንሣኤው እንሰበሰባለን " - ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ
ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት የ2017 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከመልዕክታቸው የተወሰደ ፦
" የትንሣኤ በዓል የክርስቲያን ሕይወት መሠረትና ምሶሶ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ትንሣኤ ባይኖር እምነታችን ከንቱ በሆነ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ የሚታዘንልን ሰዎች በሆንን ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክቱን የጻፈው በቆሮንጦስ ክርስቲያኖች መካከል ትንሣኤን የሚጠራጠሩ ሰዎች ስለነበሩ ነው፤ በሌላ አነጋገር ትንሣኤን እየካዱ ወይንም እየተጠራጠሩ ክርስቲያን ነን ማለት ትርጉም እንደሌለው እያስተማረ ነበር ማለት ነው፡፡
ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረ ጌታ አሁንም ሰውን በትንሣኤው አዲስ ፍጥረት አደረገው፡፡ ሰውን በመልኩና በአምሳሉ መፍጠሩ ብዙ ያስተምረናል፡፡ የተለየ ቦታና ሃላፊነት ለሰው እንደተሰጠ ያሳየናል፡፡ ትንሣኤው ደግሞ ሰውን በሙሉ በድጋሚ ወደ አንድ ማምጣቱን ያሳየናል። ትንሣኤ በሰው ውድቀት የተጨማደደውን መልክ ያስተካክላል፡፡ ትንሣኤ ሁሉንም ነገድ፤ ሁሉንም ቋንቋ፤ ሁሉንም ባህል ወደ አንድ ያመጣዋል፡፡ ትንሣኤ የጎደለውን ይሞላል፡፡ የተረሳውን ያስታውሳል፡፡ የሕይወትን ወሳኝ ጥሪ ወደ ትክክለኛው ቦታ ይመራዋል፡፡
የትንሣኤዉ የምሥራች ከምንም በላይ የምርምር ውጤት ሳይሆን የእምነት ፍሬ ነገር መሆኑንም ማስተዋል ያሻል፡፡ ትንሣኤን መስበክ የተቀበሉትን እምነት ማስተላለፍ ነውና፡፡
ቅዱሳት መጽሐፍ ስናነብና ስናሰላስል በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ብርሃን የምናይበት ወቅት ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሰውን ልጅ ታሪክም ሆነ የራሳችንን ታሪክ እንዲሁም በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ብርሃን ልንቃኘው ያሻል፡፡ በዚያን ወቅት አዲስ መረዳትን እናገኛለን፡፡ ዘመናችንን በልዩ ብርሃን እንረዳለን፡፡ የታሪክ ትርጉማችንንም ይቀይራል፤ ለሕይወትም የምንሰጠው ትርጉም ሙላትና በረከት ይኖረዋል፡፡ ምናልባት መልስ ያጣንባቸው እንቆቅልሾች መልስ ያገኛሉ፡፡ ሐዋርያት ክርስቶስን እስከ ቀራንዮ ድረስ መከተል ከብዷቸው ሸሽተው ነበር፡፡ በድፍረት ወጥተው መመስከር የቻሉት በትንሣኤውና በጰራቅሊጦስ ምስጢር የተነሣ ነው፡፡ ቀራንዮና የመስቀል ሞት ያለትንሣኤ አሁን ያለውን ትርጉም ባላገኙ ነበር፡፡ የወንጌል የምሥራች የተገለጠው በክርቶስ ትንሣኤ ነው፡፡
ብዙ የሚያስጨንቁና የሚያሳዝኑ ነገሮች በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ያጋጥሙናል፡፡ የሰው ጥበብ እስከተወሰነ ድረስ ያደርሰን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጌታችንን በመከተል ብቻ የሚገኙ በረከቶች አሉ፡፡
የተፈጠርንበትን ዓላማ ስንስት ወደ መሠረታዊው ዓለም የሚመልሰን ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡
መከፋፈል፤ መድሎ፤ ምቀኝነት፤ ጭካኔ የተፈጠርንበት ዓለም አይደሉም፡፡ አፍራሽ ሐሳብ፤ ጎጂ ንግግርና ተግባር ከተፈጠርንበት ዓላማ እጅግ የራቁ ነገሮች ናቸው፡፡ እውነተኛ መፍትሔዎች የሚመጡት ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ወደ መስቀሉ ስንቀርብ ወደ ትንሣኤውም እንቀርባለን፡፡ መስቀል መሸሸጊያችን ሲሆን ትንሣኤም እንዲሁ አምባችን ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በመስቀልና በትንሣኤው አማካኝነት አዲስ ኪዳንን፤ አዲስ ፍጥረትን፤ እውነተኛ እርቅን አምጥቷልና ነው፡፡
በመስቀልና በትንሣኤው የተሰበረው ይጠገናል፤ የደከመው ይበረታል፤ የወደቀው ይነሣል፤ የተሸነፈው ያሸንፋል ይህንንም ለማክበር በትንሣኤው እንሰበሰባለን፡፡ የአምልኮ ሥርዓታችን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ የተመሠረተ ነውና፡፡ "
(የአባታችን ሙሉ መልዕክት ከላይ ተያይዟል)
@tikvahethiopia
#Tigray
በቀድሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት በሦስት ጀነራሎች ላይ የተቀመጠው ጊዚያዊ እግድ በአዲሱ ፕሬዜዳንት ተሽሯል።
በአራተኛው ጀነራል የተወሰነው ከሃላፊነት የማንሳት ውሳኔም ተሰርዟል።
የቀድሞ ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ፦
- በጀነራል ምግበይ ሃይለ
- በጀነራል ዮውሃንስ ወ/ጊዮርጊስ
- በጀነራል ማሾ በየነ መጋቢት 1/2017 ዓ.ም ጊዚያዊ የእግድ ደብዳቤ መፃፋቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ ፈንታ በአቶ ጌታቸው ረዳ በተፃፈ ደብዳቤ ከስራ ገበታቸው እንዲነሱ መወሰኑ ይታወሳል።
በቀድሞ ፕሬዜዳንት የተቀመጠው ጊዚያዊ እግድና ከስራ የማሰናበት ውሳኔ በአዲሱ የጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ሌ/ጀነራል ታደሰ ወረደ ሙሉ በሙሉ ተሰርዟል።
አዲሱ ፕሬዜዳንት ሚያዝያ 9/2017 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ ጊዚያዊ እግዱና የስራ ስንብቱ ከመሰረዛቸው በተጨማሪ ፤ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊው በስራ ገበታቸው እንዲቀጥሉ የሚያፅና የሹመት ደብዳቤ ፅፈዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መቐለ
#TikvahEthiopiaFamilyMekelle
@tikvahethiopia
የትንሳኤ ሎተሪ ወጣ።
የ2017 ዕጣ ዛሬ በኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት በዕድል አዳራሽ መውጣቱን የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት አሳውቋል።
በዚህም ፦
1ኛ ዕጣ ቁጥር 0312160 ➡️ 10,000,000 ብር (አስር ሚሊዮን ብር)
2ኛ ዕጣ ቁጥር 0302606 ➡️ 5,000,000 ብር (አምስት ሚሊዮን ብር)
3ኛ ዕጣ ቁጥር 0269838 ➡️ 2,500,000 (ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ብር)
4ኛ ዕጣ ቁጥር 1301182 ➡️ 1,500,000 ብር (አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ብር)
(ሙሉ የዕጣ ማውጫ ዝርዝር ከላይ ተያይዟል)
@tikvahethiopia
በM-PESA ታላቅ የበዓል ቅናሽ!
የበዓል ግብይታችንን በM-PESA እንክፈል፣ 10% ተመላሽ እናግኝ!
እና ምን እንጠብቃለን ሸመት ሸመት እናድርግ!
#MPESAEthiopia #MPESASafaricom
🔈 #የሰራተኞችድምጽ #ከሰም
" ሰራተኞቹ ከስራ የተሰናበቱበት መንገድ ከህግ ውጭ በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንቅስቃሴ ተጀምሯል " - የሰራተኞች ማህበር ሊቀ መንበር
በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት የከሰም ስኳር ፋብሪካ ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰራተኞቹን የ2 ወር ማስጠንቀቂያ በመስጠት የሥራ ውላቸው እንዲቋረጥ ማድረጉ ቅሬታ አስነስቷል።
ስሜ እንዳይጠቀስ ያሉን አንድ ሰራተኛ በአሁኑ ሰዓት ሰራተኞቹ በመጠለያ ጣቢያና ከዘመድ ጋር ተጠግተው እንደሚገኙ ገልጸው ለሁለት ወራት ያህል ደመወዝ ባለመከፈሉ በከፋ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
የከሰም ስኳር ፈብሪካ የሰራተኞች ማኅበር ሊቀ መንበር አቶ ጌታሁን አርፊጮ በበኩላቸው ፈብሪካው ሰራተኞችን ከስራ ያሰናበተበት መንገድ ከህግ አግባብ ውጭ በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ለመውሰድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።
የከሰም ስኳር ፈብሪካ የሰራተኞች ማኅበር ሊቀ መንበር አቶ ጌታሁን በዝርዝር ምን አሉ ?
" ፋብሪካው ሰራተኞችን ሲያሰናብት የሁለት ወር ማስጠንቀቂያ ማለትም ሚያዚያ 10/2017 ዓ.ም የሚያበቃ ውል በመስጠት ነው።
ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም በመጀመሪያ ሰራተኞችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመበተን አማራጮችን መመልከት ነበረበት።
በአማራጭነትም ወደ ሌሎች መስሪያ ቤቶች አዘዋውሮ ማሰራት ወይም እዛው ግቢ ውስጥ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ሰብሎችን እያመረቱ እንዲቆዩ ማድረግ ይችል ነበር።
ፋብሪካው ለወጭ ቅነሳ ሲል የሰራተኞችን ጥቅም አሳጥቷል መብትም ጥሷል። ሰራተኞቹ በሁለት ወር የማስጠንቀቂያ ጊዜ ከሰጠ በኃላ 1 ወር ከ14 ቀን ወደ ኃላ ተመልሰው የዓመት እረፍት እንዲሞሉ አስገድዷቸዋል።
ይህም ትልቅ የመብት ጥሰት ነው። በዚህ ወቅት ስራ ላይ ነበሩ ደሞዝም በልተውበታል ይህንን አናደርግም ያሉ ሰራተኞች በቅርብ አለቆቻቸው በግዳጅ የአመት እረፍት እንዲሞሉ ተደርገዋል።
ይህ የሆነበት ምክንያትም ሰራተኛው የዓመት እረፍቱን በገንዘብ እንዳይጠይቅ ለማድረግ ታስቦ ነው።
ሴት ሰራተኞችን በተመለከተ በአሰሪ ሰራተኛ አዋጅና በህብረት ስምምነቱ መሰረት ነፍሰጡር በሆኑበት ሰዓትና ወልደው አራት ወር እስኪሞላቸው ድረስ ከስራ አይቀነሱም ይላል ይህ ህግ ግን ተጥሷል።
ማስጠንቀቂያ አሰጣጡም ህግን የተከተለ አይደለም። በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ መሰረት አንድ ዓመት ያገለገለ የ 1 ወር ማስጠንቀቂያ ይኖረዋል።
እስከ 9 አመት ላገለገለ 2 ወር ከ9 አመት በላይ ላገለገል 3 ወር የማስጠንቀቂያ ይሰጠው ነበር ፋብሪካው ግን ይህንን አላደረገም።
ፋብሪካው የሰራተኞችን ቅነሳ ሲሰራ ከሰራተኛ ማኅበሩ ጋር መነጋገር ሲገባው ብቻውን ወስኖ ሰራተኞቹን አሰናብቷል፤ ይህንን የመብት ጥሰት በመያዝ ወደ ህግ ለመሄድ እንቅስቃሴ ተጀምሯል " ብለዋል።
ሊቀመንበሩ እነዚህንና ሌሎች ጥያቄዎችን በመያዝ ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ቢሮ ፤ ለኢትዮጵያ ኢንቭስትመንት ሆልዲንግ፤ ለከሰም ስኳር ፈብሪካ አመራር ቦርድ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ነገር ግን ምላሽ የሚሰጣቸው አካል አንዳላገኙ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያም የከሰም ስኳር ፋብሪካ ስራ አስኪያጅን አቶ አሊ ሁሴን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ስልኩ ባለማንሳታቸው አስተያየታቸውን ማካተት ለጊዜው አልቻለም።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ በተቋሙ በኩል ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
ፎቶ ፦ ዕለተ አርብ " ስቅለት " በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን በጾም ፣ በጸሎት እና ስግደት ሥነ ሥርዓት እየተከበረ ነው።
ሐዋርያዊት ጥንታዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን ፤ ጌታዋ እስከመስቀል ሞት ድረስ የከፈለላትን መከራና ዋጋ በማሰብ ነው የዛሬውን ቀን (ስቅለት) በመላው ዓለም በሚገኙት አብያተ ክርስቲያኗ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በጾም በጸሎትና በስግደት የምታከብረው።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
Photo Credit : AMN
@tikvahethiopia
" የሉካንዳ ያልሆኑ ግለሰቦች ይዘው ሲመጡ በልዩ ሁኔታ ከ11 ሰዓት (ከበዓሉ ጠዋት) ጀምሮ የእርድ አገልግሎት እንሰጣለን " - ቄራዎች ድርጅት
ማህበረሰቡ የትንሳዔ በዓልን በሚያከብርበት ወቅት በሕጋዊ ቄራዎች የታረዱ እንስሳት ስጋን በመጠቀም እንዲሆን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አሳሰበ።
ለበዓሉ የእርድ አገልግሎት ዝግጅትን ምን ይመስላል ? በሚል ቲክቫህ ኢትዮጵያ የጠየቅናቸው የድርጅቱ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አታክልቲ ገ/ሚካኤል፣ " በበዓላት በርከት ያሉ እንስሳት በልዩ ሁኔታ እንደሚገቡ ይጠበቃል። ዘድሮም ወደ 6,500 እንሰሳት ይገባሉ። ትላልቅ እንስሳት ወደ 4,000፤ ትናንሽ የምንላቸው በግና ፍየል ደግሞ 2,500 ይገባሉ ብለን እንጠብቃለን " ብለዋል።
" ለነዚህ ዝግጅት ተደርጓል። አንዱ የሰው ኃይል ዝግጅት ነው። 1,000 የሰው ኃይል ሰራተኛም ለዚህ በዓል በተጨማሪ የቀጠርንበት፣ ባለፈው ፆም ወቅትም የአቅም ግባታ ስልጠናዎችን የሰጠንበት፣ የእርድ ቦታና እንስሳት የሚቆዩበት ቦታ ዝግጅት ያደረግንበት ሁኔታዎች አለ " ሲሉ ገልጸዋል።
" በስርጭት ክፍልም ችግር እንዳይጋጥም ከ40 በላይ መኪና ዝግጁ ተዘጋጅቷል። ሌሎች ተጨማሪ ድጋፍ ሰጪ ተሽከርካሪዎችም አሉ " ብለዋል።
የእርድ አገልግሎቱ መቼና ስንት ሰዓት ነው የሚከናወነው ? ለሚለው ጥያቄያችን " ሉኳንዳዎች ያውቁታል ሰዓቱን። የሉካንዳ ያልሆኑ ግለሰቦች ይዘው ሲመጡ በልዩ ሁኔታ ከ11 ሰዓት (ከበዓሉ ጠዋት) ጀምሮ የእርድ አገልግሎት እንሰጣለን " ብለዋል።
" ምርመራ አድርገን፣ እስከ ቤት አድርሰን የአገልግልት ክፍያ 1,500 ብር ነው የምናስከፍለው ለበሬ " ሲሉም ገልጸዋል።
አቶ አታክልቲ፣ " ሕገ ወጥ እርድ ዘርፈ ብዙ ችግር ስላለው ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር በሕጋዊ ቄራዎች የታረዱ እንስሳት ስጋን እንዲጠቀም ጥሪ አስተላልፋለሁ " የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
" ድርጅቱ በመጀመሪያ የነበረ አቅሙ ከ300 በታች ነበር የሚያርደው አሁን በቀን ከ3,500 እሰሳት በላይ የማረድ አቅም አለው " ሲሉም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለ66 ዓመታት ንጽህናው በሐኪም የተረጋገጠ የእንስሳት እርድ አገልግሎት አየሰጠ የመጣና የሚገኝ ተቋም መሆኑንም አመልክተዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvaEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
#YonatanBTFurniture
የትንሣኤ በአል በእርስዎ ቤት ውስጥ ልዩ ትርጉም ያለው የማይረሳ ይሆናል።
በአሉን ምክንያት በማድረግ በሁሉም የቤት እቃዎቻችን ላይ 💰ከ10% - 25%💰 እውነተኛ ቅናሸ ማድረጋችንን በታላቅ ደስታ እንገልፃለን። ይምጡ የወደዱትን የቤት እቃ የግልዎ ያድርጉ‼️
🎯ከ1984 ጀምሮ
🌐 የማህበራዊ ገጾቻችንን ይቀላለቀሉ
Telegram 👉 Telegram/yonatanbtfurniture
Facebook 👉 Facebook/yonatanbtfurniture
Instagram 👉 Instagram/yonatanbtfurniture
TikTok 👉 yonatanbtfurniture?is_from_webapp=1&sender_device=pc">TikTok/yonatanbtfurniture
📍አድራሻችን
1. ፒያሳ እሪ በከንቱ ቢቲ ታወር (ከኢቲዮ ሴራሚክ ዝቅ ብሎ)
2. ከዊንጌት አደባባይ አለፍ ብሎ ከአቢሲኒያ ባንክ ፊትለፊት
3. ከሲኤምሲ አደባባይ ወደ አያት መንገድ መሪ ሳይደርስ (ዘመን ባንክ አጠገብ)
☎️ ይደውሉልን
+251957868686
+251995272727
+251993828282
#China #USA
ቻይና ዶናልድ ትራምፕ የጣሉትን ታሪፍ ተከትሎ አገራት ከአሜሪካ ጋር በሚያደርጉት የንግድ ድርድር ወቅት አሜሪካን የምትፈልገውን በማድረግ ለማስደሰት እንዳይሞክሩ አስጠነቀቀች።
የቻይና ንግድ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት ዋሺንግተን መንግሥታት ወደ አሜሪካ የሚልኳቸው ምርቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲሆኑላቸው ከቤይጂንግ ጋር በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ላይ ጫና ለመፍጠር ማቀዷ ከተሰማ በኋላ ነው።
የትራምፕ አስተዳደር ከንግድ አጋሮች ጋር ታሪፍን በተመለከት ንግግር መጀመሩ ተገልጿል።
ትራምፕ በጥር ወር ሥልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ የጣሉ ሲሆን ሌሎች በርካታ የዓለም አገራትም ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።
የቻይና የንግድ ሚኒስትር ቃል አቀባይ " ለማስደሰት የሚደረግ ጥረት ሠላምን አያመጣም፤ እንዲሁም ማመቻመች ክብርን አያቀዳጅም " ብለዋል።
" ቻይና ሁሉም አካላት ከፍትሃዊነት ጎን መቆም አንዳለባቸው ታምናለች. . . እንዲሁም ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት እና የንግድ ሕጎች እንዲሁም የአገራት የንግድ ሥርዓትን መከላከል አለባቸው " ሲሉ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት ዎል ስትሪት ጆርናል አሜሪካ ታሪፍን በተመለከተ ከአገራት ጋር በምታደርገው ድርድር ከቻይና ጋር በሚኖራቸው ንግድ ላይ አዲስ ገደብ በመጣል ጫና ለማድረግ እንደምትፈልግ ዘግቧል።
@tikvahethiopia
#SafaricomEthiopia
✝️ እንኳን ለበአሉ በሰላም አደረሳችሁ! ሰሞኑን ከምንወዳቸው ጋር እየተገናኘን እናሳልፍ! ለቀን፣ለሳምንት እና ለወር የሚያገለግሉ ያልተገደበ የዳታ ጥቅሎችን በ50% ቅናሽ አዘጋጅተንላችኋል! መልካም በአል!
#SafaricomEthiopia #Easter #Furtheraheadtogether
ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በብጹዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሕልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
@tikvahethiopia
ፖፕ ፍራንሲስ አረፉ።
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን ቫቲካን አሳውቋል።
@tikvahethiopia
#Tigray
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ እንደ አዲስ የተዋቀረው የጊዚያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ስራ እንደጀመረ ተነግሯል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ ሲመራ የነበረውን የካቢኔ ቁጥር ከ27 ወደ 21 ፤ ሁለት ምክትል ፕሬዜዳንት የነበረውን ወደ አንድ እንዲወርድ ያደረጉት ፕሬዜዳንቱ እስካሁን ምክትላቸው ማን እንደሆነ በይፋ አላስታወቁም።
ይሁን እንጂ ከደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የህወሓት ሃይል ሰፊ ቁጥር ያለው የካቢኔ አባል ያካተቱ ስለመሆኑ ተነግሯል።
ምክትላቸው የህግ ምሁርና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ኣማኒኤል አሰፋ አደርገው መሾማቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ጨምሮ በርካቶች በመፃፍ ላይ ይገኛሉ።
አንዳንዶች " አዲሱ የጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት የወጣቱ የለውጥ ጥያቄ የሚመልስ አዲስ ካቢኔ አላዋቀሩም " በሚል ነቄፌታ እያቀረቡ ይገኛሉ።
ፕሬዜዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ አዲሱ ካቢኔ ስራ መጀመሩን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ " ትግራይ በአሸናፊና ተሸናፊ የፓለቲካ ቅኝት ከገባችበት አዘቅት መውጣት አትችልም " ብለዋል።
" ባለፉት ሁለት የጊዚያዊ አስተዳደሩ ዓመታት በርካታ ጥሩና መጥፎ ነገሮች ተፈፅመዋል " ሲሉ ገልጸዋል።
" ጥሩውን ለራስ መጥፎውን ለሌላ መስጠት አይቻልም ድሉም ውድቀቱም የጋራ ነው ከእልህና ህዝብንና አገር ከሚጎዳ ፓለቲካዊ አካሄድ እንውጣ " ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
" የቀድሞ ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳና ሌሎች የጊዚያዊ አስተዳደር አመራሮች የሚመሰገኑበት መድረክ ይዘጋጃል " ያሉት ፕሬዜዳንቱ ጥሪውን ተቀብለው እንዲገኙ ከወዲሁ በይፋ የግብዣ ጥሪ አቅርበዋል።
የቀድሞ ፕሬዚዳንትና አመራሮች ይመሰገኑበታል የተባለው የምስጋና ስነስርዓት መቼ እና የት እንደሚዘጋጅ የተባለ ነገር የለም።
በሌላ በኩል ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ተፈናቃዮች የሚገኙበት ስቃይና ሰቆቃ ባወሳ ንግግራቸው " በዚሁ ዓመት ወደ ቄያቸው የመመለስ ስራ ይሰራል ፤ በማቆያ ጣብያ የሚቆዩት ደግሞ አኗኗራቸው እንዲሻሻል ትኩረት ይደረጋል " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መቐለ
@tikvahethiopia
#ሐኪሞች🙏
በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞች የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ በሀዋሳ ከተማ ለህግ ታራሚዎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ሰጥተዋል።
የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ ጤና ተቋማት የተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች በሀዋሳ ከተማ በሚገኘዉ የማረሚያ ተቋም በመገኘት ለህግ ታራሚዎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ሰጥተዋል።
በነፃ የህክምና አገልግሎቱ አጠቃላይ ሀኪሞች ፣የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ፣ የቆዳ ህክምና ስፔሻሊስት ፣ የጥርስ ሀኪሞች እና የዓይን ህክምና ስፔሻሊስት ተሳትፈውበታል።
ባለሙያዎቹ በሀዋሳ ከተማ ማረሚያ ተቋም በመገኘት ከ358 ለሚሆኑ የህግ ታራሚዎች ነፃ የምርመራና የህክምና አገልግሎት ሰጥተዋል።
ባለሙያዎቹ ከአዲስ አበባ የመጡ ሲሆኑ የዘጠነኛዉ ሺ ሲትኮም ተከታታይ ድራማ ደራሲና ዳይሬክተር ዶክተር በዛብህ ብርሃኑ መረሃ ግብሩን መምራታቸውን ላለፉት ሶስት ቀናት የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን ለመስማት ችለናል።
@tikvahethiopia
" አንዳችን በሌላችን ላይ ያስከተልነው ጉዳት ጥላቻን ከትውልድ ወደ ትውልድ ከማሸጋገር እና የህዝባችንን ሰቆቃ ከማራዘም በስተቀር አንዳችም መልካም ነገር አላስገኘልንም " - ቄስ ደረጀ ጀምበሩ
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሀፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ የ2017 ዓ/ም የትንሣኤ በዓልን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከመልዕክታቸው የተወሰደ ፦
" የትንሣኤን መታሰቢያ በዓል ስናከብር እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ታላቅ ፍቅርና ከዚህም የተነሳ አንድያ ልጁን ስለ እኛ ሃጥያት ለመስቀል ሞት አሳልፎ መስጠቱን እንድናስብ ግድ ይለናል። ይህም ከዘላለም ሞት ወደ ዘላለም ሕይወት መሸጋገራችንን ፤ ከሃጥያት ባርነት ነጻ መውጣታችንን በመገንዘብ እግዚአብሔርን ይበልጥ እንድናመሰግነውና ዕለት ዕለትም በቅድስና እንድናመልከው ሊያደርገን ይገባል።
ስለሆነም ፋሲካችን የሆነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ከሃጥያታችን ስለዋጀን የመንግሥቱም ወራሽ በመሆን በጽኑ ተስፋ ተደላድለን እንድንቆም ስላደረገን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ብቻ ይሁን።
ትንሣኤ ጥላቻ በፍቅር ፤ መለያየት በአንድነት ፤ ሀዘን በደስታ የተቀየረበት የእግዚአብሔር ድንቅ ፍቅር የተገለጠበት ስለሆነ ከሁሉ በፊት በእኛ በክርስቲያኖች መካከል እውነተኛ ፍቅር መታየት ይኖርበታል።
ትንሣኤ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተራራቁ የሚቀራረቡበት እንዲሁም በያለንበት ታርቀን በማስታረቅ መልካም ምሳሌነታችን ጎልቶ እንዲታይ ያስፈልጋል። ይህ ከሁሉም ምዕመናን የሚጠበቅ መልኮታዊ ትዕዛዝ ስለሆነ ቸል የምንለው ጉዳይ አይሆንም።
.
.
ሀገራችን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የእርስ በእርስ ግጭቶች የተነሳ ብዙ ጎዳቶችን እንዳስተናገደች የሚካድ አይደለም። በዋናነት ለድህነታችን እና ወደኃላ ለመቅረታችን ምክንያቱ ልዩነቶችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ መሳሪያ በማንሳት መጠፋፋት ላይ በማተኮራችን እንደሆነ ግልጽ ነው።
አንዳችን በሌላችን ላይ ያስከተልነው ጉዳት ጥላቻን ከትውልድ ወደ ትውልድ ከማሸጋገር እና የህዝባችንን ሰቆቃ ከማራዘም በስተቀር አንዳችም መልካም ነገር አላስገኘልንም። ይህ እየታወቀ አሁንም ከመጠፋፋት አዙሪት ለመውጣት የምናሳየው ፍቃደኝነት አለመኖር ወይም አዝጋሚ መሆን እጅግ ያሳዝናል።
የችግራችን መፍትሄ ያለው በእኛው እጅ ስለሆነ ችግሩ ተባብሶ የበለጠ ጉዳት ሳያስከትል ቆም ብለን ልናስብ ያስፈልጋል። በፍጹም ቅንነት መከባበር እና መደማመጥ በእርቅ የሀገራችንን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ እና የህዝባችንንም አንድነት በፅኑ አለት ላይ ለማቆም መወያየት ግድ ይለናል።
ስለዚህ አሁንም ካውንስላችን የሰላም ጥሪውን በመደጋገም ሲያስተላልፍ በእግዚአብሔር ስም ነው። "
(የአባታችን ሙሉ መልዕክት በዚህ ተያይዟል ፦ https://youtu.be/WPX_OADik1Q?si=-raFopdEdxRCCpRa)
@tikvahethiopia
" መሳሪያ አንሥታችሁ እርስ በርስ በመገዳደል የምትገኙ ወገኖቻችን እባካችሁ ቆም ብላችሁ ኣስቡና ሰላምና ዳቦ ኣጥቶ ለተቸገረው ሕዝባችሁ ስትሉ ለሰላማዊ መፍትሔ ዕድል ስጡ " - ቅዱስነታቸው
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2017 ዓመተ ምሕረት የትንሣኤ በዓልን በማስመልከት አባታዊ ቃለ በረከት አስተላልፈዋል።
ከመልዕክታቸው የተወሰደ ፦
" ዘር ሳይኖር ፍሬ እንደማይገኝ ሁሉ ሕይወታዊ ትንሣኤም ያለ ሃይማኖትና ሥነ - ምግባር ሊገኝ ኣይችልም፡፡ ጌታችንም ይህንን ኣስመልክቶ ሲያስተምረን " መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ይነሣሉ፤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ " ብሎ ኣሳውቆናል፡፡
ከዚህ አኳያ የሕይወትን ትንሣኤ የሚያገኝ ያመነ፣ የተጠመቀና መልካም ስራን የሰራ እንጂ የተነሣው ሁሉ ኣለመሆኑ ግልጽ ነው፤ መነሣቱ ሁሉም የግድ ይነሣል፤ ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ የሚጠብቀን ሕይወት በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ሳለን በሰራነው ስራ የሚወሰን እንደሆነ ጌታችን በማያሻማ ሁኔታ ኣረጋግጦልናል፡፡
ስለሆነም የመጨረሻው ዕድላችን የተንጠለጠለው እምነትን ተከትለን በምንሰራው ስራ ላይ መሆኑን ለኣፍታ እንኳ መዘንጋት የለብንም፤ ዛሬ ከሰው ኣእምሮ በእጅጉ እየራቀ የሚገኘው ይኸው እምነትና ሥነ-ምግባር ነው፤ ሰዎች ከእምነትና መልካም ሥነ-ምግባር በራቁ ቊጥር ሕይወት መራራ እንድትሆን ትገደዳለች፡፡
እኛ ኢትዮጵውያን ከጥንት ጀምሮ በእምነትና ሥነ-ምግባር እየተመራን፣ በደልን በይቅርታ እየዘጋን፣ እስከ ጋብቻ በሚዘልቅ ባህለ-ዕርቅ ደምን እያደረቅን፣ በወንድማማችነት ፍቅር ተስማምተን በሺሕ ለሚቆጠሩ ዘመናት እንዳልኖርን፣ እነሆ ዛሬ ለታላቅነታችን በማይመጥን ሆናቴ መለያየትና መጣላት ብሎም እርስ በርስ መገዳደል ዕለታዊ ተግባራችን ኣድርገን እንገኛለን፡፡
ይህ በጣም ኣሳዛኝ ክሥተት ነው፤ ይህንን ሳናስተካክል የምናከብረው በዓለ ትንሣኤም እዚህ ግባ የሚባል ደስታ ሊያስገኝልን እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡
እየሆነ ያለው ሁሉ ማንንም ኣይጠቅምም፤ በዕርቅ፣ በይቅርታና በውይይት የማይፈታ ችግር ያለ ይመስል ይህን ያህል መጨካከን እንዴት እንደ መፍትሔ ተደርጎ ይወሰዳል ? አሁንም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የምንማፀነው ፡- እባካችሁ እኛው ራሳችን ሸምጋይና ተሸምጋይ ሆነን ችግሮቻችንን ለመፍታት በብርቱ እንስራ፤ መፍትሔም እናምጣ፤ መሳሪያ ኣንሥታችሁ እርስ በርስ በመገዳደል የምትገኙ ወገኖቻችን እባካችሁ ቆም ብላችሁ ኣስቡና ሰላምና ዳቦ ኣጥቶ ለተቸገረው ሕዝባችሁ ስትሉ ለሰላማዊ መፍትሔ ዕድል ስጡ።
ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኗን በትክክል የሚያረጋግጥ ሰላማዊ መፍትሔ በማስቀመጥ ለአንድነትዋና ለዕድገትዋ አጥብቃችሁ ጣሩ ፤ ግጭትና መለያየት ከሚያጠፋን በቀር ምንም ዓይነት ጥቅም ሊሰጠን እንደማይችል ብዙ ማብራሪያ የሚያስፈልገው ኣይደለም፤ ስለሆነም ገዳዩን መሳሪያ ኣስቀምጡና በሃይማኖት፣ በኣንድነት፣ በስምምነትና በጭንቅላት ኃይል ሰላምን ኣምጡ፤ ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ጥሪ ነው።
በልዩ ልዩ ምክንያት ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው በየኣካባቢው በረኃብ ኣለንጋ እየተገረፉ የሚገኙት ወገኖቻችን በትንሣኤው በዓል ተጽናንተውና እፎይ ብለው በደስታ እንዲያሳልፉ ካለን ከፍለን በመመገብና በማልበስ እንድንደርስላቸው በእግዚአብሔር ስም ኣባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን። "
(የቅዱስነታቸው ሙሉ የትንሣኤ በዓል መልዕክት ከላይ ተያይዟል)
@tikvahethiopia
#Update : በማይናማር ' ዲኬቢኤ ' ካምፕ የነበሩ 252 ኢትዮጵያውያን ትላንት ለታይላንድ የቀረበች በማይናማር በምትገኝ ማይዋዲ ወደምትባል ከተማ መሻገራቸውን፣ ይህም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የሚያስችላቸው አንድ እርምጃ መሆኑን የወላጆች ኮሚቴ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።
በዚህም፣ ኢትዮጵያውያኑንና የሌሎች ሀገራት ዜጎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 276 ወጣቶችን የዲሞክራቲክ ካረን ጦር ወደ ማይዋዲ እንደላከ ኮሚቴው ነግሮናል።
ኢትዮጵያውኑ በማይናማር በሚገኘው የዲሞክራቲክ ካረን ጦር (ዲኬቢኤ) ሥር የነበሩ፣ በመጀመሪያ ወደ ታይላንድ እንዲያሻግራቸው፣ ከዚያ ወደ ሀገራቸው እንዲመልሳቸው የመንግስትን ምላሽ ደጋግመው ሲጠይቁ የነበሩ ናቸው።
ኮሚቴው " አሁንም ገና መንግስት ወደ ቦታው ወኪል መላክ አለበት። ‘ለኤንጂኦ ውክልና ሰጥተናል’ ነው ያሉት ግን በኤንጂኦ ውክልና ብቻ ተላልፈው ወደ ኢትዮጵያ መተላለፍ አይችሉም። ለዚህ ጉዳይ የመንግስት ደሊጌሽን ያስፈልጋል " ብሏል።
" በተጨማሪም፣ በማይናማር ቢጄኤፍ ካምፕ ስክሪን አውት ተደርገው፣ ፓስፓርት ተሰጥቷቸው የተቀመጡ ወደ 495 ኢትዮጵያውያን አሉ። እንዲሁም የመንግስትን ሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ሦስት ልጆች በስቃይ ናቸው የዛሬዎቹ ልጆቻቸን ከወጡበት አካባቢ ያሉ ማለት ነው " ሲል አክሏል።
" ከዚህ ቀደም ልጆቻችን በአንድ ወቅት ከካምፕ ባመለጡበት ወቅት በፓሊስ ታግተው የተመለሱ ወደ 26፣ በቢጂኤፍ ካምፕ አካባቢም ሌሎች 14 ልጆቻችን በስቃይ ላይ ናቸው። የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው ያሉት " ብለዋል።
" ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳውቀናል። ልጆቹን ከነሙሉ ስማቸውና ከነፓስፓርት ቁጥራቸው አስተላልፈናል። ‘ለሁለቱም ኤምባሲዎች እናሳውቃለን’ ብለውናል " ሲል ኮሚቴው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
#ዮናታን_ቢቲ_ፈርኒቸር
በዓሉን ምክንያት በማድረግ በሁሉም የቤት እቃዎቻችን ላይ ከ10% - 25% እውነተኛ ቅናሸ ማድረጋችንን በታላቅ ደስታ እንገልፃለን።
መጪው የትንሣኤ በዓል በእርስዎ ቤት ውስጥ ልዩ ትርጉም ያለው የማይረሳ ይሆናል።
ይምጡ የወደዱትን የቤት እቃ የግልዎ ያድርጉ❗️❗️
እስከ ቅዳሜ 1 ሰዓት አገልግሎት እንሰጣለን
ከ1984 ጀምሮ
የማህበራዊ ገጾቻችንን ይቀላለቀሉ
Telegram Telegram/yonatanbtfurniture
Facebook Facebook/yonatanbtfurniture
Instagram Instagram/yonatanbtfurniture
TikTok yonatanbtfurniture?is_from_webapp=1&sender_device=pc">TikTok/yonatanbtfurniture
አድራሻችን
1. ፒያሳ እሪ በከንቱ ቢቲ ታወር (ከኢቲዮ ሴራሚክ ዝቅ ብሎ)
2. ከዊንጌት አደባባይ አለፍ ብሎ ከአቢሲኒያ ባንክ ፊትለፊት
3. ከሲኤምሲ አደባባይ ወደ አያት መንገድ መሪ ሳይደርስ (ዘመን ባንክ አጠገብ)
ይደውሉልን ፦ +251957868686 / +251995272727 / +251993828282
#ዮናታን_ቢቲ_ፈርኒቸር
" የ12ኛ ክፍል ፈተና ከአንድ ወር / ከአንድ ወር ተኩል በኃላ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው " - ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከአንድ ወር / ከአንድ ወር ተኩል በኃላ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ ፥ " ይሄ አራተኛው ነው በአዲሱ የፈተና አሰጣጥ ፈተና የሚሰጥበት " ብለዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ባለፉት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከትምህርት ቤቶች ወጥቶ ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አስገብቶ ፈተና እንዲሰጥ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ስለዘንድሮው የ2017 ዓ/ም ፈተና በተናገሩበት ወቅት 150 ሺህ ተማሪዎች ፈተናቸውን በኦንላይ እንዲወስዱ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ፥ " እንደ ከዚህ ቀደሙ አድካሚ በሆነ ከቦታ ቦታ ልጆችን እያዘዋወሩ ከመሄድ ባለፈው ዓመት 29 ሺህ ተማሪ ነበር ኦንላይን ፈተና የሰጠነው ዘንድሮ ደግሞ 150 ሺህ ተማሪ ኦንላይን ፈተና ለመስጠት እየተዘጋጀን ነው " ብለዋል።
ሚኒስትሩ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥበትን ቀን ቆርጠው ባይናገሩም ፈተናው ከአንድ ወር / ከአንድ ወር ተኩል በኃላ እንዲሰጥ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
#Update
#የጤናባለሙያዎችድምጽ
" የሆስፒታሉን ሜዲካል ዳይሬክተር ጨምሮ 14 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች እና አስተዳደር ሰራተኞች ከስራ ቦታቸዉ ተወስደው ታስረዋል " - የሀንጣጤ ሆስፒታል ባለሙያዎች
" ' ለሚዲያ መረጃ ስለሰጣችሁ ሚዲያ የሚከፍላችሁ መስሏችኋል ' የሚሉ አመራሮችም አሉ ! "
በሲዳማ ክልል፤ ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ሎካ አባያ ወረዳ በሚገኘዉ ሀንጣጤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ከ8 ወራት በላይ የትርፍ ሰዓት ክፊያ ባለመከፈሉ ለሎካ አባያ ወረዳ፣ ለማዕከላዊ ሲዳማ ዞንና ለሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ በደብዳቤ ካሳወቁ በኋላ የትርፍ ሰዓት ስራ ማቆማቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ማሳወቃቸው ይታወሳል።
በወቅቱ ስለ ጉዳዩ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የማዕከላዊ ሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መንግስቱ ማቴዎስ ፥ የሠራተኛዉ ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑን ገልፀዉ ክፍያዉ እንዲፈፀም ከክልሉ መንግስት ብድር መጠየቃቸዉንና በቅርቡ እንደሚከፈላቸዉ ገልፀዉ የነበረ ሲሆን " የትርፍ ሰዓት ስራ ማቆም መብታቸዉ ነዉ " ሲሉ ገልጸውም ነበር።
ትላንት የሆስፒታሉ ሠራተኞች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደገለፁት " ሁሉም ሰራተኛ በአንድነት ተፈራርሞ ባስገባዉ ደብዳቤ መሰረት ከባለፈዉ ሳምንት ጀምሮ የትርፍ ሰዓት ስራ ብቻ ያቆሙ ቢሆንም የሆስፒታሉን ሜዲካል ዳይሬክር እና 7 የማኔጀመንት አካላትን ጨምሮ 14 የሚሆኑ የሆስፒታሉ ባለሙያዎችን ፖሊስ ከስራ ቦታቸዉ ጭምር ወስዶ አስሯቸዋል " ብለዋል።
" ሁሉም ሠራተኛ የትርፍ ሰዓት ስራ ማቆሙ ሰበብ ተደርጎ በመደበኛ ስራዉ ላይ እንከን እንዳይፈለግበትና ላለመከሰስ የስራ ሰዓቱን በአግባቡ እየተጠቀመ ነዉ " የሚሉት ሠራተኞቹ " ትላንት ጠዋት በድንገት 2 ዶክተሮች፣ 7 ነርሶችንና ሌሎች ባለሙያዎችን 'ትፈለጋላችሁ' በሚል ያለ ፍርድ ቤት መጥሪያ ከነ ጋዎናቸዉ ጭምር ወደ ሀንጣጤ ፖሊስ ጣቢያ አስገብተዋቸዋል " ሲሉ ገልፀዋል።
" ሁሉም የሆስፒታሉ ሠራተኞች አንድ ላይ በመሆን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ብንሄድም ' ከበላይ አካላት ታዘን ነዉ ' የሚል ምላሽ ነዉ የተሰጠን " ብለዋል።
ሠራተኞቹ ቀኑን ሙሉ እዛዉ ለመሆን መወሰናቸዉንና ከአስራ አንድ ሰዓት በኋላ የተወሰኑ አመራሮች ወደ ፖሊስ ጣቢያ የመጡ ቢሆንም የታሰሩት ሳይፈቱ ወደ ' ቤታችሁ ሂዱ ' ተብለው እስኪጨላልም እዛዉ የቀሩ ባለሙያዎች እንደነበሩ አስረድተዋል።
" የትርፍ ሰዓት ክፍያ ካልተከፈለን ብለን ስራ አላቆምን " የሚሉት የጤና ባለሙያዎቹ " አይደለም መደበኛ ስራ ለማቆም ምንም ሳይከፈለን በብዙ ችግሮች ዉስጥ ሆነን እራሳችንን እየጎዳን ከ8 ወራት በላይ የትርፍ ሰዓቱን ስራ ጭምር ስንሰራ ቆይተናል ነገሮች ከአቅማችን በላይ ሲሆኑ በደብዳቤ አሳዉቀን የትርፍ ሰዓቱን ስራ ለማቆም ተገደናል " ብለዋል።
ሁሉም ሠራተኛ የትርፍ ሰዓት ስራ ባቆመበት ሁኔታ የሆስፒታሉን ሜዲካል ዳይሬክተር ጨምሮ የማኔጅመንት አባላትንና የተወሰኑ ሠራተኞችን ለይቶ የማሰሩ ጉዳይ ተገብነት የሌለው እና የሚመለከታቸዉ አካላት በአፋጣኝ እልባት ሊሰጡበት የሚገባ ጉዳይ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
" ' ሚዲያ ላይ ስለከሰሳችሁ ሚዲያ የሚከፍላችሁ መስሏችኋል' የሚሉ አመራሮች ነበሩ " ያሉን ቅሬታ አቅራቢዎቹ " ሜዲካል ዳይሬክተሩንና ማኔጅመንቱን ' ለምን ሠራተኛ ታሳምፃላችሁ፣ ከወረዳዉና ከዞኑ መንግስት የሚተላለፍላችሁን መመሪያ ለምን አታስፈፅሙም ' ብለዉ የሚያስፈራሩም ነበሩ " ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስታዉቀዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የከፍተኛ አመራሮችን ምላሽ ለማግኘት ጥረት አድርጓል።
ከዚህ ቀደም የማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መንግስቱ ማቴዎስ በስልክ መረጃ የሰጡን ቢሆንም አሁን ላይ " ወደ ቦታዉ በአካል ካልመጣችሁ መረጃ መስጠት አልችልም " በማለታቸዉ ሳይሳካ ቀርቷል።
ፈቃደኛ ሲሆኑ ምላሻቸዉን የምናካትት ይሆናል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
@tikvahethiopia
#ለጥንቃቄ
" በተለይ ነጋዴዎች ቢዚ የሚሆኑባቸው ስቶሮች/ሱቆች አካባቢ የወንጀል ፈፃሚዎች ትኩረት ነው " - ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ
በትንሳዔ የበዓል ግብይት ወቅት ሸማቾችና ነጋዴዎች ከህገ ወጥ የገንዘብ ኖቶች መጭበርበር እንዲሁም ከምግብና መጠጥ ጋር ከሚቀላቀሉ ባዕድ ነገሮች ራሳቸውን እንዲጠብቁ የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል አሳሰበ።
በህገወጥ ወጥ የብር ኖት ከመጭበርበር ማህበረሰቡ በምን መልኩ ሊድን ይችላል ? ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ? ማጭበርበሩ የሚፈጸመውስ በምን ሁኔታ ነው ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ኮሚሽኑን ጠይቋል።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ምን መለሱ ?
“ በበዓል ሰሞን ከሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች መካከል አንዱ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ነው። ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሩ በሁለት መልኩ ነው በገበያ ላይ እንቅስቃሴ የሚያደርገው።
አንዱ፥ ሙሉ ለሙሉ ህገ ወጥ የሆኑ የገንዘብ ኖቶች ወደ ገበያ ሊመጡ ይችላሉ። ወይን ደግሞ ህጋዊ ከሆኑት ጋር በመቀላቀል ህነ ወጥ የገንዘብ ኖቶች ወደ ገበያ ሊመጡ ይችላሉ።
ስለዚህ በተለይ ነጋዴዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። በተመሳሳይ ሸማቾችም ከነጋዴዎች የሚቀሉትን አረጋግጠው መቀበል ይኖርባቸዋል።
በተለይ ነጋዴዎች ቢዚ የሚሆኑባቸው ስቶሮች/ሱቆች አካባቢ የወንጀል ፈፃሚዎች ትኩረት ነው። እዚያ አካባቢ መጥተው አጭበርብረው ከሌሎች ሰዎች ገንዘቡን ሰጥተው ሊሄዱ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
ስለዚህ ነጋዴው ገንዘብ የሚቀበል ራሱን የቻለ አንድ ሰው፣ ቁሳቁሶቹን ለሸማች የሚሰጥ ደግሞ ሌላ ሰው አድርጎ በጥንቃቄ መገበያዬት ያስፈልጋል። ካልሆነም ዲጂታል የክፍያ አማራጮችን መከተልም ተቀባይነት አለው ” ብለዋል።
ኮማንደሩ በሚበሉና በሚጠጡ ነገሮች መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምን አሉ ?
“ የሚበሉና የሚጠጡ ነገሮች ላይ ባዕድ ነገሮችን ቀላቅሎ ማምጣት በተለይ በበዓል ሰሞን ቁጥሩ ከፍ ይላል ተብሎ ይገመታልና በተቻለ አቅም ሸማቾች የሚገዟቸውን ለበዓል የሚጠቀሟቸው እንደ ዘይት፣ ቅቤ፣ በበሬና የመሳሰሉ ነገሮችን በጥንቃቄ መገብዬት እንዳለባቸው ለማስታወስ እንወዳለን።
በእምነት ተቋማት፣ በዋና ዋና አደባባዮች በሰፈሮች አካባቢ ጠንካራ የወንጀሎች መከላከል ሥራ እንሰራለን። ህብረተሰቡ ግን አጠራጣሪ ነገር ካየ በ 0111110111 እና በ 991 መረጃ በመስጠት ተባባሪ መሆን አለበት ” ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ የአዲስ አበባ ፓሊስ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሥራ ገብቷል። በዓሉን የሚመጥን ትልቅ ዝግጅት ተደርጓል። በበዓሉ ከሚሰማራው የወንጀልና የትራፊክ መከላከል አባላት ባሻገር በበዓሉ ቴክኖሎጂዎችን እንጠቀማለን። በተለያዩ የመገበያያ ቦታዎች የፓሊስ ጥበቃ እናደርጋለን ” ነው ያሉት።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
" ስቅለት "
በክርስትና አስተምሮ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለ በደል ያለ ጥፋት ንጹሕ እና ጻድቅ የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰቀሉበት ዕለት ነው።
ዕለቱ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ዂሉ መድኀኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልዕልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የሚታሰብበት ታላቅ ቀን ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን #በስግደት እና #በጾም የሚታሰብ ሲሆን በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረትም በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች ታስቦ ይውላል፡፡
በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከንጋታው ጀምሮ እስከ ማምሻው በዕለቱ የተፈጸሙትን ክስተቶች በሰዓት ከፍላ በልዩ መንፈሳዊ ሥርዓትና በስግደት ታከብረዋለች ፦
✝ ዓርብ ጠዋት
ዓርብ ጠዋት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጲላጦስ ፊት በፍርድ አደባባይ መቆሙ ይታሰባል። የካህናት አለቆችና ሕዝቡ ሽማግሎች ሁሉ ሊገድሉት በኢየሱስ ላይ ተማከሩ፤ አስረውም ወሰዱት ፥ ለገዢው ለጰንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት።
✝ በ3 ሰዓት
ጲላጦስ በወቅቱ በነበረው ሕዝብ ግፊት መሠረት ወንጀለኛውን በርባንን ከእስር አስፈትቶ በምትኩ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠበት፤ አካሉ እስኪያልቅም 6,666 የገረፉት ከሊቶስጥራ - ቀራኒዮ እርጥብ መስቀል አሸክመው የወሰዱበት ነው።
✝ በ6 ሰዓት
ኢየሱስ ክርስቶስን እጆቹን እና እግሮቹን ቸንክረው በቀራንዮ ጎልጎታ ተራራ በ2 ወንበዴዎች መካከል የተሰቀለበት ነው።
✝ በ9 ሰዓት
በእምነቱ አስተምሮ ይህ ሰዓት ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ከሥጋው በባሕርይ ሥልጣኑ የለየበት ወደ ሲዖል ወርዶም የታሠሩትን ሁሉ ያስፈታበት ነው።
✝ 11 ሰዓት
ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብር እና ሐዘን ጋር በአዲስ መቃብር የቀበሩበት ነው።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
@tikvahethiopia
ነፃ የትምህርት ዕድል !
የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ)
በፋሽን ዲዛይን የትምህርት ዘርፍ ለመሰልጠን ፍላጎት ያለው/ያላት
ለመመዝገብ የሚያስፈልጉ ሰነዶች ፦
ዕድሜ : ከ 18 እስከ 29 ዓመት
ፎቶ ፡ አምስት (5) ጉርድ ፎቶ
የቀበሌ መታወቂያ
የድጋፍ ደብዳቤ ፡ በክፍያ መማር አለመቻልን የሚያሳይ የድጋፍ ደብዳቤ ከወረዳ
የትምህርት ደረጃ ፡ 8ኛ ክፍል እና ከዚያ በላይ
የምዝገባ ጊዜ ከመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ/ም እስከ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ/ም
አድራሻ ፡ መስቀል ፍላወር፣ ቅዱስ ያሬድ ቤተክርስቲያን ፊት፣ ዶንቦስኮ ገዳም አጠገብ (ወደ ግራ 100 ሜትር ገባ ብሎ)
ለበለጠ መረጃ፡ 0114160640 / 0920568912
ስልጠናውን ላጠናቀቁ ሰልጣኞች የራሳቸውን ስራ/ቢዝነስ ለመጀመር የገንዘብ ድጋፍ ይሰጣቸዋል!
ሴት አመልካቾች ይበረታታሉ
(ወወክማ)