"እኔም ይመለከተኛል"
ታላቅ አገልግሎት የማስፋት ዘመቻ
እንደምን አላችሁ የተወደዳችሁ ኦርቶዶክሳዊያን የዝማሬ ዳዊት ቤተሰቦች እና ተከታታዮች።
የዝማሬ ዳዊት ቻናላችን ለ5 ዓመታት ከእናንተ ጋር ሲያገለግል እና ቃለ እግዚአብሔርን ሲያስተላልፍ እንደነበር ይታወቃል።
ከቅርብ ግዜ ጀምሮ ደግሞ በዩቲዩብ ላይም ኦርቶዶክሳዊያንን ያማከለ ትምህርት በቪድዮ ስንሰጥ ቆይተናል።
አሁንም በእዚህ በጥቅምት ወር የዩቲዩብ ቻናሉን በአዳዲስ ርዕሶች ትምህርት ልንጀምር ስለሆነ ይህን አገልግሎት የማስፋት ዘመቻ መሳተፍ የእያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ የውዴታ ግዴታ ነው።
💻የዩቲዩብ ዘመቻ🖥
በሚል ርዕስ የዩቲዩባችንን አባላት ለማሳደግ እና ሰብስክራይበር ለመጨመር ሥራ ስለጀመርን።
ሁላችሁም ይህ ቻናላችን ወደ ተሻለ እድገት እንዲደርስ እና ቃለ እግዚአብሔርም በስፋት እንዲዳረስ አንድ አሻራ ሁላችንም እናሳርፍ።
👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇
https://bit.ly/2O1Z3d8
https://bit.ly/2O1Z3d8
https://bit.ly/2O1Z3d8
👆👆👆👆👆👆👆👆👆👆👆👆👆
ይህንን ሊንክ በመጫን ወደ ዩቲዩባችን ገጽ ትገባላችሁ ከእዛም ሰብስክራይብ(Subscribe) በማድረግ ቪድዮዎቹን እንድታዩ እና የዘመቻው አንድ አካል እንድትሆኑ እንጠይቃለን።
"እኔም ይመለከተኛል"
እግዚአብሔር አምላክ አገልግሎታችንን ይባርክ✝
#የቀጠለ
ቅዱስ አቡነ አረጋዊ ለተራራው ፍቅር አደረባቸው፤ አለቀሱም፡፡ በዚህም ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ዳግመኛ መጥቶ ‹‹አረጋዊ ሆይ አይዞህ! አትፍራ ስልጣን ተሰጥቶሃልና፡፡ በሐረጓ በስተቀኝ በኩል ባለችው ቦታ ተቀመጥ፤ ወደ ተራራው ጫፍ ያወጣህ ዘንድ በገመድ ፋንታ ቁመቱ ስድሳ ክንድ የሆነ ታላቅ ዘንዶ እግዚአብሔር ይልክልሃል›› አለው፡፡ ከዚያም በጾም በጸሎት ሁለት ሱባኤ ይዘው ፲፬ ቀን በዚያ ተቀመጡ፡፡ የታዘዘውም ዘንዶ በሦስት ሰዓት መጣ፤ በዘንዶው ጅራት ላይ ወጥቶ በቅጽበት ከተቀደሰው ተራራ ጫፍ ላይ ደረሰ፤ እንደደረሰም ሦስት ጊዜ ሰገደ። ወዲያው ‹‹ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ›› እያለ አመሰገነ፡፡ ስለዚህም ቦታው ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሎ ተሠየመ፡፡ በመሸም ጊዜ አነስተኛ ዳቦ አንስቶ ባርኮ መብላት ጀመረ፡፡ ዳቦዋ ግማሽ ስትሆን ስለጠገበ የዳቦውን ግማሽ አምሳል ለኋለኛው ትውልድ ምልክት ትሆን ዘንድ እንጨት ጠርቦ/ቀርጾ/ አስቀመጠ፤ ይህች ምልክት እስከዛሬ ድረስ አለች፡፡
ደቀ መዛሙርቱም ከታች ወደ ላይ የሚወጡበትን መሰላል በሠሩ አባታችን አቡነ አረጋዊ ደግሞ መጠነኛ ቤት ሠራና ይዞት የመጣውን ታቦት በውስጡ አስገባ፡፡ እግዚአብሔርንም ስለቁርባኑ ወይም ስለመሥዋዕቱ ለመኑ፡፡ እግዚአብሔርም ልመናቸውን ሰምቶ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ መላእክት ከሰማይ ይዘውላቸው ወረዱ፡፡ ለመኖሪያቸውም ትንሽ በአት አገኙ፡፡ ያለምንም መኝታ በጸሎትና በስግደት በመትጋት ተቀመጡ፡፡ በዚያም ብዙ ተአምራትን አደረጉ፤ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘው የሚሠቃዩትን በጸሎታቸው ኃይል ፈወሷቸው፤ ያላመኑትን ደግሞ እያስተማሩ አሳመኗቸው፤ ለዚያችም ሀገር ብርሃን አበሩላት።
አፄ ካሌብም ‹‹አባቴ ሆይ! በጸሎትህ አስበኝ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት ግዳጅ ትፈጽማለች፤ ኃይልም ታሰጣለች፤ በጠላት ላይም ድልን ታቀዳጃለች›› ብሎ አቡነ አረጋዊን ለመኗቸው፤ ወደ ደቡብ በሄደም ጊዜ የመን ከሠራዊቱ ጋር ዘምተው አሸንፈው ተመለሱ። የአፄ ካሌብ ልጅ ገብረ መስቀል ቤተ ክርስቲያን ሠራላቸው። በውስጡም በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም የተሰየመች በወርቅና በብር ያጌጠች ታቦት አስገባ፡፡ ንጉሥ አፄ ገብረ መስቀል ከተራራው ላይ ሲወርድ ለቤተክርስቲያኑ ማሠሪያ የሆነውን መወጣጫ መሰላል ‹ላፍርሰው› ብሎ አባታችንን ጠየቀ፤ አባታችንም ‹‹አዎ! አፍርሰው፤ አትትወው፤ ነገር ግን ስለዘንዶው ጅራት ፈንታ ሰዎች ይወጡበት ዘንድ ገመድ አብጅ›› አለው፡፡ ንጉሡም አባታችን አቡነ አረጋዊ እንዳዘዘው አደረገ፤ያም ቦታ ደብረ ደኃምሞ ተብሎ ተሰየመ።
ከዚህ በኋላም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት ተገልጾ ‹‹ከድካም ወደ ዕረፍት፣ ከኃዘን ደስታ ወዳለበት፣ ከኀሣር ወደ ክብር ቦታ በታላቅ ደስታ እወስድህ ዘንድ ወደ አንተ መጣሁ፡፡ የሞት ጥላ አያርፍብህም፤ መልአከ ሞትም ሊያስደነግጥህ አይችልም፤ እንደ ነቢያት ኤልያስና ሄኖክ ትሰወራለህ›› ብሎ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ አረገ፡፡
አባታችን አቡነ አረጋዊ ማትያስ ለተባለው ደቀ መዛሙር ጌታችን ተገልጦ የሰጣቸውን ቃል ኪዳንና ይህ መጽሐፍ ተጽፎ ለልጅ ልጅ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ነገሩት፤ (መዝ ፻፲፩/፻፲፪፥፮) ወንድሞቹ ደቀ መዛሙርቶቹ በተሰበስቡበትም ሁሉንም ከአስተማሩ በኋላ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ በሥጋ አታዩኝም›› አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም በመሪር ኃዘን እግራቸው ሥር ወድቀው አለቀሱ፤ አባታችን አቡነ አረጋዊም አጽኗኗቸው፡፡ ጥቅምት ፲፬ ቀን ቅዱስ አባታችን አቡነ አረጋዊ በ፺፱ ዓመታቸው ተሰወሩ፤ በዚያም ከመቋሚያና ከመስቀል በስተቀር ምንም የተገኘ የለም፡፡
የአባታችን አብነ አረጋዊ ረድኤት በረከት በሁላችንም ላይ ይደር! አሜን
ለወዳጅዎ ሼር ያድርጉ!
💚 @ortodoxmezmur 💚
💛 @ortodoxmezmur 💛
❤️ @ortodoxmezmur ❤
እንኳን ለአባታችን አቡነ አረጋዊ አመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሰን! ጥቅምት 14
መምህር ሸዋገኘሁ ከበደ
አባታችን አቡነ አረጋዊ ከዘጠኙ ቅዱሳን አባቶች አንዱ ናቸው። ትውልዳቸውም ከሮም ነገሥታት ወገን ሲሆን አባታቸው ይስሐቅ የሮም ንጉሥ ነበር፤ እናታቸው እድና ትባላለች፡፡ ሁለቱም እግዚአብሔርን የሚፈሩና የሚያከብሩ ነበሩ፡፡ የተባረከ ልጅም ወለዱ፤ በሕገ እግዚአብሔርና ቅዱሳት መጻሕፍትን እያነበበ አደጉ፡፡ ለአቅመ አዳም ሲደርሱ ሚስት ቢታጭላቸውም ከነበራቸው የክርስቶስ ፍቅር የተነሳ ትዳር መመሥረትን ትተው ደውናስ ወደ ምትባል ገዳም ሔዱ፤ በዚያም አባ ጳኩሚስ ይኖሩ ነበር።
አበምኔቱ አባ ጳኩሚስን ልበሰ ምንኩስናን እንዲያለብሳቸው ጠየቁት። አባ ጳኩሚስም ‹ልጄ ሆይ አንተ የንጉሥ ልጅ እንደ መሆንህ መጠን የመንግሥቱ ወራሽ ነህና መንኩሰህ ለመኖር ይቻልሃልን?› አለው፡፡ ቅዱስ አባታችንም ‹‹አባቴ ሆይ የምድር መንግሥት ኃላፊ ጠፊ ነው፤ ነገር ግን የማታልፈውንና የማትጠፋውን ዘለዓለማዊት መንግሥት እወርስ ዘንድ እፈልጋለሁ›› አለው፡፡ እናም በ፲፬ ዓመታቸው በአባ ጳኩሚስ እጅ የምንኩስናውን ልብስ ለበሱ፤ በገዳሙም እየተጉ ኖሩ፡፡
ከዚህ በኋላ የጻድቁ ዜና በሀገራቸው ሮም ውስጥ እንዲሁም በመላው ቦታ ተሰማ፡፡ በዚህም የተማረኩት ሰባት ቅዱሳን፤ አባ ሊቃኖስ ከቁስጥንጥንያ፣ አባ ይምአታ ከቆስያ፣ አባ ጽሕማ ከአንጾኪያ፣ አባ ጉባ ከቂልቅያ፣ አባ አፍፄ ከእስያ፣ አባ ጰንጠሌዎን ከሮም፣ አባ አሌፍ ከቂሳርያ እርሱ ወዳለበት ገዳም መጡ። አባ ጳኩሚስ ለብዙ ዓመታት ምንኩስናን ሥርዓተ ማኅበርን አስተማራቸው። እናቱ ንግሥት እድና የልጅዋን ዜና ሰምታ እርሱ ወዳለበት መጥታ መነኮሰች፡፡ በሴቶችም ገዳም ገብታ መኖር ጀመረች፡፡ መነኮሳቱም አባ ዘሚካኤልን መሪያቸው አደረጉት፤ በአካለ ሥጋ ሕፃን ሆኖ ሳለ የአእምሮውን ብስለት ዐይተው የሕይወት መንገድ ስለመራህን አቡነ አረጋዊ መባል ይገባሃል አሉት፤ በዚህም አቡነ አረጋዊ ተብለው ተጠሩ፤ ብልህ አዋቂ ማለትም ነው፡፡
በገዳመ ዳውናስ ሰባት ዓመት ከቆዩ በኋላ ይስሐቅን (በኋላ አባ ገሪማን) ለመጠየቅ እና የሀገሩን ሰዎች ለማስተማር በአንድነት ሆነው ወደ ሮም ተመልሰው ሲያስተምሩ በዘመናቸው የካቶሊክ ሃይማኖት እንዲቀበሉ ጫና ቢደረግባቸውም… ‹‹እውነቱን እውነት፣ ሐሰቱን ሐሰት ማለት ተገቢ ነውና ክርስቶስ ከተዋሕዶ በኋላ ሁለት ባሕርይ ነው ብሎ ማስተማር ክሕደት ነው››…. ብለው በድፍረት መቃወም ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ በኃይል እና በገንዘብ ብዛት የምትመካው የሮማ ቫቲካን ቤተክርስቲያን ቅዱሱን ማሳደድ ጀመረች:: ቅዱሱ አባታችን አቡነ አረጋዊም ‹‹በአንዱ ቦታ መከራ ቢያጸኑባቸው ወደ ሌላው ሽሹ…›› የሚለውን የወንጌል ቃል አብነት በማድረግ እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም የዐስራት ሀገር እንዲሆናት በቃል ኪዳን እንደሰጣት ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበቡ በኢትዮጵያ ፍቅር ተያዘ፤ ወደዚያውም መሄድ ፈለገ፡፡ ይህንንም ሁለት ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ለማንም ሳያሳውቅ ቅዱስ ሚካኤል እየመራው ንጉሡና ጳጳሱ ካሉበት አክሱም ከተማ ደረሰ፡፡
እዚያም ጥቂት ቀን ተቀምጦ ወደ ሮም ተመለሰ፡፡ ስለኢትዮጵያ በዐይኑ የተመለከተውን በጆሮ የሰማውን ሁሉ ለወንድሞቹ ነገራቸው፡፡ እነርሱም ‹‹እኛም ወደዚህች ሀገር መሄድ አለብን›› ተባባሉ፡፡ ያላቸውን የመገልገያ ዕቃ ይዘው ከታቦቶቻቸውና ከካህናቶቻቸው ጋር ንዋየ ቅድሳትና መጻሕፍችን ይዘው ከመሰል ወገኖቻቸው ጋር አባታችን ዘሚካኤል (በአቡነ አረጋዊ) እየመራቸው በአልዓሜዳ አምስተኛ የንግሥና ዓመት በ፬፻፹ ዓ.ም ንጉሡና ጳጳሱ ካሉበት አክሱም ከተማ ደረሱ፤ ስምንቱ ቅዱሳንም መጡ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ዘጠነኛው አቡነ ይስሓቅ (አቡነ ገሪማ) በሮም ከነገሠ ከሰባት ዓመት በኋላ መንግሥቱን ትቶ ወደ አክሱም መጣ፤ በዚያን ጊዜ እንደነሱ አመነኮሱት፤ ቍጥራቸውም ዘጠኝ ሆነ።
ለሁሉም አንድ የተለየ ማረፊያ ቦታ ቤተ ቀጢን የተባለው ተሰጥቷቸው በጸሎት ተጠምደው ይኖሩ ነበር፤ በአንዲት የጸሎት ቤት በአንድነት ሆነው ለጸሎት ፈጣሪያቸውን እየለመኑ፤ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረጉም ቆዩ፡፡ መላእክት ዘወትር ባለመለየት ያጽኗኗቸው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዘወትር ይገለጽላቸው ነበር፡፡ በእያንዳንዳቸውም ብዙ ተአምራት ተደረጉ፡፡ ከእነርሱ መካከልም ተራራ ያፈለሱ፣ ባሕሩን ከፍለው ደረቅ መንገድ ያደረጉ፣ ስንዴ ዘርተው በቅጽበት ለዘጠኝ ሰዓት መሥዋዕተ ቁርባን ያደረሱ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምድር በእነዚህ የቅዱሳን ኪደተ እግር ተቀደሰች፡፡
በኋላም ንጉሥ አልዓሜዳ ከሞተ በኋላ በነገሠው በታዜና ስድስተኛ ‹‹የንግሥና ዓመት ላይ ተለያይተን እናስተምር›› ብለው ወስነው ተለያዩ። አቡነ ሊቃኖስ ደብረ ቆናጽል፣ አባ ጰንጠሌዎን ከእዚሁ ሁለት ምዕራፍ እልፍ ብሎ ከሚገኝ ኮረብታ፣ አቡነ ይስሐቅ መደራ፣ አቡነ ጉባ በእዚሁ በመደራ ትይዩ ሦስት ምዕራፍ እልፍ ብሎ፣ አባ ጽሕማ፣ አባ ይምዓታ ገርዓልታ፣ አባ አሌፍ አሕስዓ ብሕዛ በተባለችው፣ አባ አፍጼ ይሐ ተሠማሩ።
አባታችንም እናታቸው እና ማትያስ የተባለ ደቀ መዝሙራቸውን ይዘው ከሁሉም ርቀው ወደ መረጡት ቦታ ሲሄዱ ከዛፍ ጥላ ሥር አረፉ፤ እርስዋም እስከ ዛሬ ድረስ የቅዱሳን ማረፊያ ሆና ትገኛለች፡፡ አባታችንም ቅድስት ቦታ ዳሞን ባያት ጊዜ ሦስት ጊዜ ሰገደ፡፡ በተራራዋ ሥር ለመኖርም ወደደ፡፡ ነገር ግን ወደ ተራራዋ መውጫ አላገኘም፡፡ ተመልሶ ወደ ሌላ ተራራ ሄዶ አማረጠ፤ ሆኖም እንደ ደብረ ዳሞ የበረከት ቦታ ባላገኘ ጊዜ ተመልሰ፡፡ በዚያም የምንጭ ውኃ አገኘ፡፡ ውኃውን እየተንከባከበች የሴት መነኮሳቶችን ታስተዳድር ዘንድ እናቱ ቅድስት እድናን አስቀመጣት፤ ይህችንም ደብረ በአተልሞ አላት፤ ትርጓሜውም የእናቴ ማረፊያ ቤት ማለት ነው፡፡
ከዚያም ሲሄድ ጠፍጣፋ ድንጋይ አገኘና ከዚያ ላይ ትንሽ ምንጣፍ አነጠፈና ተቀመጠ፡፡ በትሩንም በድንጋይዋ ላይ አቆመ፡፡ በተነሳም ጊዜ ደቀ መዝሙሩ ማትያስ በትሩንና ምንጣፉን ሲያነሳው ያች ድንጋይ ቁመቷም ጎኗም ልክ በዚያች ምንጣፍ አይነት ቅርጽ አወጣች፡፡ የቀድሞ መልኳ ነጭ ሲሆን አሁን ግን የማይፋቅና የማይላጥ ቀይ ቀለም ሆኗል፡፡ ስለአባታችን አቡነ አረጋዊ ታላቅነቱና ስለክብሩ ከዚያ የደረሱ ሁሉ ይሳለሟታል፡፡
ከዕለታት በአንደኛው ቀን መንገድ ሲሄድ ውሎ ከተራራ አጠገብ ወደ ታች የተንዠረገገች ሐረግ/ገመድ/ አገኘና በሥሯ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ሲጸልይ ከቆየ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦ ‹‹እግዚአብሔር ያከበረህ ቅዱስ ሆይ ምን ያስጨንቅሃል?›› አለው፡፡ አባታችንም ‹‹ከዚህ ተራራ ላይ ወጥቼ ስለኃጢአቴ ይቅርታን እጠይቅህ ዘንድ እወዳለሁ›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹ወደ ተራራው የምትወጣበትን እግዚአብሔር እስኪልክልህ ድረስ ጥቂት ጊዜ ታገስ›› አለው፡፡
#ይቀጥላል
ለወዳጅዎ ሼር ያድርጉ!
💚 @ortodoxmezmur 💚
💛 @ortodoxmezmur 💛
❤️ @ortodoxmezmur ❤