ortodoxmezmur | Неотсортированное

Telegram-канал ortodoxmezmur - ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

134932

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። . ዝማሬ ዳዊት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አስተምህሮና ስርዓትን የጠበቁ ትምህርቶች, መዝሙራት እና ወረባትን ከነዜማቸው ለማግኘት ቻናላችንን ይጎብኙ። ለማንኛውም ሀሣብ, ጥቆማ, አስተያየት @zmaredawit_messengerbot ላይ ቢያስቀምጡልን ይደርሰናል

Подписаться на канал

ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​እንኳን ለአባታችን አቡነ አረጋዊ አመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሰን! ጥቅምት 14

መምህር ሸዋገኘሁ ከበደ

አባታችን አቡነ አረጋዊ ከዘጠኙ ቅዱሳን አባቶች አንዱ ናቸው። ትውልዳቸውም ከሮም ነገሥታት ወገን ሲሆን አባታቸው ይስሐቅ የሮም ንጉሥ ነበር፤ እናታቸው እድና ትባላለች፡፡ ሁለቱም እግዚአብሔርን የሚፈሩና የሚያከብሩ ነበሩ፡፡ የተባረከ ልጅም ወለዱ፤ በሕገ እግዚአብሔርና ቅዱሳት መጻሕፍትን እያነበበ አደጉ፡፡ ለአቅመ አዳም ሲደርሱ ሚስት ቢታጭላቸውም ከነበራቸው የክርስቶስ ፍቅር የተነሳ ትዳር መመሥረትን ትተው  ደውናስ ወደ ምትባል ገዳም ሔዱ፤ በዚያም አባ ጳኩሚስ ይኖሩ ነበር።

አበምኔቱ አባ ጳኩሚስን ልበሰ ምንኩስናን እንዲያለብሳቸው ጠየቁት። አባ ጳኩሚስም ‹ልጄ ሆይ አንተ የንጉሥ ልጅ እንደ መሆንህ መጠን የመንግሥቱ ወራሽ ነህና መንኩሰህ ለመኖር ይቻልሃልን?› አለው፡፡ ቅዱስ አባታችንም ‹‹አባቴ ሆይ የምድር መንግሥት ኃላፊ ጠፊ ነው፤ ነገር ግን የማታልፈውንና የማትጠፋውን ዘለዓለማዊት መንግሥት እወርስ ዘንድ እፈልጋለሁ›› አለው፡፡ እናም በ፲፬ ዓመታቸው በአባ ጳኩሚስ እጅ የምንኩስናውን ልብስ ለበሱ፤ በገዳሙም እየተጉ ኖሩ፡፡

ከዚህ በኋላ የጻድቁ ዜና በሀገራቸው ሮም ውስጥ እንዲሁም በመላው ቦታ ተሰማ፡፡ በዚህም  የተማረኩት ሰባት ቅዱሳን፤ አባ ሊቃኖስ ከቁስጥንጥንያ፣ አባ ይምአታ ከቆስያ፣ አባ ጽሕማ ከአንጾኪያ፣ አባ ጉባ ከቂልቅያ፣ አባ አፍፄ ከእስያ፣ አባ ጰንጠሌዎን ከሮም፣ አባ አሌፍ ከቂሳርያ እርሱ ወዳለበት ገዳም መጡ። አባ ጳኩሚስ ለብዙ ዓመታት ምንኩስናን ሥርዓተ ማኅበርን አስተማራቸው። እናቱ ንግሥት እድና የልጅዋን ዜና ሰምታ እርሱ ወዳለበት መጥታ መነኮሰች፡፡ በሴቶችም ገዳም ገብታ መኖር ጀመረች፡፡ መነኮሳቱም አባ ዘሚካኤልን መሪያቸው አደረጉት፤ በአካለ ሥጋ ሕፃን ሆኖ ሳለ የአእምሮውን ብስለት ዐይተው የሕይወት መንገድ ስለመራህን አቡነ አረጋዊ መባል ይገባሃል አሉት፤ በዚህም አቡነ አረጋዊ ተብለው ተጠሩ፤ ብልህ አዋቂ ማለትም ነው፡፡

በገዳመ ዳውናስ ሰባት ዓመት ከቆዩ በኋላ ይስሐቅን (በኋላ አባ ገሪማን) ለመጠየቅ እና የሀገሩን ሰዎች ለማስተማር በአንድነት ሆነው ወደ ሮም ተመልሰው ሲያስተምሩ በዘመናቸው የካቶሊክ ሃይማኖት እንዲቀበሉ ጫና ቢደረግባቸውም… ‹‹እውነቱን እውነት፣ ሐሰቱን ሐሰት ማለት ተገቢ ነውና ክርስቶስ ከተዋሕዶ በኋላ ሁለት ባሕርይ ነው ብሎ ማስተማር ክሕደት ነው››…. ብለው በድፍረት መቃወም ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ በኃይል እና በገንዘብ ብዛት የምትመካው የሮማ ቫቲካን ቤተክርስቲያን ቅዱሱን ማሳደድ ጀመረች:: ቅዱሱ አባታችን አቡነ አረጋዊም ‹‹በአንዱ ቦታ መከራ ቢያጸኑባቸው ወደ ሌላው ሽሹ…›› የሚለውን የወንጌል ቃል አብነት በማድረግ እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም የዐስራት ሀገር እንዲሆናት በቃል ኪዳን እንደሰጣት ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበቡ በኢትዮጵያ ፍቅር ተያዘ፤ ወደዚያውም መሄድ ፈለገ፡፡ ይህንንም ሁለት ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ለማንም ሳያሳውቅ ቅዱስ ሚካኤል እየመራው ንጉሡና ጳጳሱ ካሉበት አክሱም ከተማ ደረሰ፡፡

እዚያም ጥቂት ቀን ተቀምጦ ወደ ሮም ተመለሰ፡፡ ስለኢትዮጵያ በዐይኑ የተመለከተውን በጆሮ የሰማውን ሁሉ ለወንድሞቹ ነገራቸው፡፡ እነርሱም ‹‹እኛም ወደዚህች ሀገር መሄድ አለብን›› ተባባሉ፡፡ ያላቸውን የመገልገያ ዕቃ ይዘው ከታቦቶቻቸውና ከካህናቶቻቸው ጋር ንዋየ ቅድሳትና መጻሕፍችን ይዘው ከመሰል ወገኖቻቸው ጋር አባታችን ዘሚካኤል (በአቡነ አረጋዊ) እየመራቸው በአልዓሜዳ አምስተኛ የንግሥና ዓመት በ፬፻፹ ዓ.ም ንጉሡና ጳጳሱ ካሉበት አክሱም ከተማ ደረሱ፤ ስምንቱ ቅዱሳንም መጡ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ዘጠነኛው አቡነ ይስሓቅ (አቡነ ገሪማ) በሮም ከነገሠ ከሰባት ዓመት በኋላ መንግሥቱን ትቶ ወደ አክሱም መጣ፤ በዚያን ጊዜ እንደነሱ አመነኮሱት፤ ቍጥራቸውም ዘጠኝ ሆነ።

ለሁሉም አንድ የተለየ ማረፊያ ቦታ ቤተ ቀጢን የተባለው ተሰጥቷቸው በጸሎት ተጠምደው ይኖሩ ነበር፤ በአንዲት የጸሎት ቤት በአንድነት ሆነው ለጸሎት ፈጣሪያቸውን እየለመኑ፤ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረጉም ቆዩ፡፡ መላእክት ዘወትር ባለመለየት ያጽኗኗቸው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዘወትር ይገለጽላቸው ነበር፡፡ በእያንዳንዳቸውም ብዙ ተአምራት ተደረጉ፡፡ ከእነርሱ መካከልም ተራራ ያፈለሱ፣ ባሕሩን ከፍለው ደረቅ መንገድ ያደረጉ፣ ስንዴ ዘርተው በቅጽበት ለዘጠኝ ሰዓት መሥዋዕተ ቁርባን ያደረሱ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምድር በእነዚህ የቅዱሳን ኪደተ እግር ተቀደሰች፡፡

በኋላም ንጉሥ አልዓሜዳ ከሞተ በኋላ በነገሠው በታዜና ስድስተኛ ‹‹የንግሥና ዓመት ላይ ተለያይተን እናስተምር›› ብለው ወስነው ተለያዩ። አቡነ ሊቃኖስ ደብረ ቆናጽል፣ አባ ጰንጠሌዎን ከእዚሁ ሁለት ምዕራፍ እልፍ ብሎ ከሚገኝ ኮረብታ፣ አቡነ ይስሐቅ መደራ፣ አቡነ ጉባ በእዚሁ በመደራ ትይዩ ሦስት ምዕራፍ እልፍ ብሎ፣ አባ ጽሕማ፣ አባ ይምዓታ ገርዓልታ፣ አባ አሌፍ አሕስዓ ብሕዛ በተባለችው፣ አባ አፍጼ ይሐ ተሠማሩ።

አባታችንም እናታቸው እና ማትያስ የተባለ ደቀ መዝሙራቸውን ይዘው ከሁሉም ርቀው ወደ መረጡት ቦታ ሲሄዱ ከዛፍ ጥላ ሥር አረፉ፤ እርስዋም እስከ ዛሬ ድረስ የቅዱሳን ማረፊያ ሆና ትገኛለች፡፡ አባታችንም ቅድስት ቦታ ዳሞን ባያት ጊዜ ሦስት ጊዜ ሰገደ፡፡ በተራራዋ ሥር ለመኖርም ወደደ፡፡ ነገር ግን ወደ ተራራዋ መውጫ አላገኘም፡፡ ተመልሶ ወደ ሌላ ተራራ ሄዶ አማረጠ፤ ሆኖም እንደ ደብረ ዳሞ የበረከት ቦታ ባላገኘ ጊዜ ተመልሰ፡፡ በዚያም የምንጭ ውኃ አገኘ፡፡ ውኃውን እየተንከባከበች የሴት መነኮሳቶችን ታስተዳድር ዘንድ እናቱ ቅድስት እድናን አስቀመጣት፤ ይህችንም ደብረ በአተልሞ አላት፤ ትርጓሜውም የእናቴ ማረፊያ ቤት ማለት ነው፡፡

ከዚያም ሲሄድ ጠፍጣፋ ድንጋይ አገኘና ከዚያ ላይ ትንሽ ምንጣፍ አነጠፈና ተቀመጠ፡፡ በትሩንም በድንጋይዋ ላይ አቆመ፡፡ በተነሳም ጊዜ ደቀ መዝሙሩ ማትያስ በትሩንና ምንጣፉን ሲያነሳው ያች ድንጋይ ቁመቷም ጎኗም ልክ በዚያች ምንጣፍ አይነት ቅርጽ አወጣች፡፡ የቀድሞ መልኳ ነጭ ሲሆን አሁን ግን የማይፋቅና የማይላጥ ቀይ ቀለም ሆኗል፡፡ ስለአባታችን አቡነ አረጋዊ ታላቅነቱና ስለክብሩ ከዚያ የደረሱ ሁሉ ይሳለሟታል፡፡

ከዕለታት በአንደኛው ቀን መንገድ ሲሄድ ውሎ ከተራራ አጠገብ ወደ ታች የተንዠረገገች ሐረግ/ገመድ/ አገኘና በሥሯ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ሲጸልይ ከቆየ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦ ‹‹እግዚአብሔር ያከበረህ ቅዱስ ሆይ ምን ያስጨንቅሃል?›› አለው፡፡ አባታችንም ‹‹ከዚህ ተራራ ላይ ወጥቼ ስለኃጢአቴ ይቅርታን እጠይቅህ ዘንድ እወዳለሁ›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹ወደ ተራራው የምትወጣበትን እግዚአብሔር እስኪልክልህ ድረስ ጥቂት ጊዜ ታገስ›› አለው፡፡

#ይቀጥላል
ለወዳጅዎ ሼር ያድርጉ!
💚 @ortodoxmezmur 💚
💛 @ortodoxmezmur 💛
❤️ @ortodoxmezmur

Читать полностью…
Подписаться на канал