-
“Let's build bridges, not walls.” Martin Luther King, Jr. — Visit my blog: https://dildiy.net/ — ድልድይ - ግላዊ እይታና ጥልቅ የመሻገሪያ እሳቤዎች የሚጋሩበት ከንባብ፣ ከኑረት እና ከምናብ የሚቀዱ ንሸጣዎች መድረክ ነው። - ሃሳቦቹ ከየትኛውም የአስተሳሰብ ጎራ (ism) አይወግኑም!! — Concern & Concept — D.S.
.
.
.
ከምከፍተው ሙዚቃ ይልቅ፣ እንዳልረብሽ የማደርገው ጥንቃቄ ከፍ ብሎ ይሰማል... ይገርማል!!
ከምጠቀመው ውሃ በላይ፣ ላለማባከን የማደርገው ጥረት ትኩረት ስቦ ያስከፋል... ምን ይባላል??
ከማበራት አምፑል በላይ፣ የመቆጠብ ልምዴ ጠያቂ ይጎትታል... ያሳቅቃል!!
ገላ ለመታጠብ 'ሻወር ቤት' ብመርጥም፣ ድንገት የገባሁ'ለት - አንኳኪ አላጣም...
በወር የምከፍለው ቁጥሩ ባይናቅም፣ 'የጨምር' ዕድገቱ አንዴም ቆሞ አያቅም...
አታምሽ ያሉኝ ፈሪ በጊዜ ብሰፍርም፣ ቤት መዋል ሲያምረኝ ግን ገላማጭ አላጣም...
.
.
.
ምክንያቱም...
👇
ያለሁት ኪራይ ቤት ነው!!
___
የአንዳንድ አከራዮች የመጀመሪያ ተግባር እንደ ሰው የሚገባህን ክብር መንጠቅ ነው... ይህንንም የሚያደርጉት ተከራይነትህን እንዳትረሳ ነው...
___
በመሰረቱ ሁላችንም ተከራይ ነን... ሰውነታችን ኪራይ ቤት ነው፣ ዓለም ኪራይ ቤት ናት፣ ተፈጥሮም እንደዚያው... አንድም ቋሚ ነገር የለም!!...
በአጭሩ - ትተነው እስከሄድን ድረስ ሁሉም ነገር ኪራይ 'ቤት' ነው...
[ታዲያ ለምንድነው - የኔ የሚባል ሳይኖርህ 'የኔ' የሚለው 'የሌለውን' የምትገፋው?...]
___
@bridgethoughts
A Beautiful Mind (2001)
Directed by Ron Howard, starring Russell Crowe as John Nash, with Jennifer Connelly in a supporting role.
_
The film is based on the life of the Nobel Prize-winning mathematician John Nash and explores his struggles with schizophrenia and his remarkable contributions to mathematics.
___
@bridgethoughts
.
.
.
ከሩቅ የሚያይህ ሰው፣ 'በኑሮዬ ጎድሏል' ብሎ የሚያስበውን፣ አልያም 'ከእኔ የተሻለ ነው' ብሎ ያመነበትን ነገር አንተ ዘንድ ስላገኘ ሊቀናብህ ይችላል...
በሩቅ 'ምታውቀው ሰው፣ ከቤቴ የለም ያልከው ኖሮት፣ አልያም ከአንተ ይልቅ በዝቶለት ስላየኸው ትቀናበት ይሆናል...
ደግሞ ሁለታችሁ፣ በሩቅ 'ምታዩት ሰው የለንም ባላችሁት ተከቦ፣ ካላችሁ በላይ ደርቦ የሚኖር ሲመስላችሁ ትቀኑበት ይሆናል...
ከሩቅ የሚያያችሁ፣ የቀናችሁበት ሰው ግን እናንተ ዘንድ ባየው ታኮ ጉድለቱን የሚያስብ ነው... የእርሱ ቤት ለሌሎች ሙላት ሆኖ እንደሚያስቀና ግን አንዳች ግንዛቤ የለውም...
አንተ ዘንድ ያለውን በሙላት ተርጎሞ የእጁን የሚያሳንስ ብዙ ተጓዥ አለ...
[ወርቅ አፈር ሆኖብህ መቸገርህን ያላየ]
የሞላለት ያልከው ብዙ እንከኑን 'ሚያስብ የሩቅ ሰው ደግሞ አለ...
[አልማዙን እንደ አመድ ሲቀበል የኖረ]
እኛ ዘንድ ያለው፣ ሁሌም ሌሎች ዘንድ ካለው አንሶ የሚታየን ነገር የኑረት እንቆቅልሽ ነው... አንዳንድ የሙላትና ጉድለት ዕይታዎቻችን 'ሃብት' እና 'ድህነት' ከምንለው ማሕበረሰባዊ መለኪያዎች ሁሉ ይሻገራሉ...
____
ለምሳሌ...
የምትወደው ሚስት አልያም አፍቃሪ ቤተሰብ ያለው የሚመስልህ አንድ ሰው ላይ ትቀና ይሆናል... ይሁንና ሰውየው የብቻነት ጉጉትና የነፃነት ናፍቆት የሚያባክነው ዓይነት ሆኖ ባንተ አኗኗር እየቀና ሊሆን ይችላል...
በመንፈሳዊ እሴቶች ተጊጠህ ስታበቃ ቁሳዊ ሃብት ባለው ሌላኛ ሰው ትቀና ይሆናል... ምናልባት ግን ባለ ቁሱ አንተ ያለህን የአዕምሮ ሰላም በማጣት ስቃይ ውስጥ እየኖረ ይሆናል...
የአካል ጉድለት ስላለብህ ብቻ በሌላው ጥንካሬና ገጽታ ትቀና ይሆናል... ይሁን እንጂ የምትቀናበት ሰው የሚጋደልበትን ስውር ጦርነት አታውቅም... ምናልባትም ሰውየው በአንተ ጽናትና የስሜት መረጋጋት የሚቀና ሊሆን ይችላል...
እይታ ነው ጎዳይ፣ አተያይ ነው ሞዪ...
___
የሰዎች 'ሙላት' የሚታየን በራሳችን 'ጉድለት' በኩል ነው... ሆኖም 'ጉድለት' የአንድ ነገር አለመኖር አይደለም... ሙላት የሚከሰትበት ስፍራ መኖሩን ማሳያ እንጂ...
የጉድለት ስሜት የንጽጽር ህመም ውጤት ነው... አንድ ጊዜ ማነፃፀር ከጀመርክ ሙላትህን ለማሰብ ዕድል አትሰጥም... ይልቁን የሌለህን ከማሰብ ስለምትጀምር ያለህን ለማየት ጊዜ ታጣለህ... ማነፃፀር የማመስገን ተነሳሽነትህን የሚሰልብ ክፉ ባላንጣ ነው...
አስታውስ -
🔔 ሙላትና ጉድለት ሁልጊዜም ተለዋዋጭ ናቸው፤
🔔 የሰዎችን ከመጋረጃ ጀርባ ያለ ትግል ሳታይ ራስህን ከእነርሱ ጋር አታነፃጽር፤
🔔 በዓይን ለማይታየው ሃብትህ ዕውቅና ከመስጠት ጀምር... [አዕምሮህ ሰላም አለው፣ የሰው ፍቅር አለህ፣ ጤነኛ ነህ፣ እጅህ ላይ የበደል ደም የለም፣ አትሰርቅም፣ አትገፋም፣ ዓላማ አለህ...]
___
በዚህ ርዕሰ ላይ Mystics የሚያስተምሩትን ጠቅልለህ ልትረዳ ብትሞክር የምታጠለው እውነት እንዲህ የሚል ነው...
"The cup is full when you recognize its emptiness. And it is empty when you ignore its fullness."
___
በነገራችን ላይ...
🐔 በሕይወትህ የት ስፍራ ነው ጉድለት የሚያቃጭልብህ?
🐔 ሌሎች አንተ ላይ የሚያደንቁት ምናልባት ትኩረት የነፈግኸው ነገርስ የለህም?...
🐔 የሌላኛውን ሰው አኗኗር ያንተን ልምምድ ለመመዘን እየተገለገልክ ይሆን?...
___
ሁላችንም የጉድለትና ሙላት ኮሮጆ ተሸክመን የምንዞር ምንዱባን ነን... ባጣነው ነገር ላይ ስናተኩር ጉድለት ያዛጋብናል... ባለን ስንደሰት ሙላት በምስጋና ይሞላናል...
___
ደቀመዝሙሩ የሱፊውን መምህር ይጠይቃል... "ለምንድነው ሌሎች ሁሉ ነገር ሲኖራቸው እኔ ብቻ ባዶነት የሚሰማኝ?"
መምህሩ አልተገረሙም... ሆኖም ጥያቄውን ከመመለሳቸው በፊት አንድ የሸክላ ማሰሮ ሰጡትና "ከወንዝ ውሃ ሞልተህ አምጣልኝ" አሉት...
ደቀመዝሙሩ እንደታዘዘው አደረገ...
ውሃ የሞላውን ማሰሮ ይዞ ከፊታቸው እንደቆመ መምህሩ ቀስ አድርገው ማሰሮውን ከስሩ ስለበሱት ውሃ መንጠባጠብ ጀመረ...
"አሁንስ ሙሉ ነው ጎደሎ?" ጠየቁት...
"ሙሉ ነው፣ ግን ደግሞ እያንጠባጠበ ነው"...
መምህሩ ፈገግ ብለው...
" እኛም እንዲሁ ነን... የሆነ ቦታ ሙላት ይሰማናል፤ በሌላ ገጽታ ደግሞ ስንጥቃት አለን - በዚያ በኩልም ጉድለት እናያለን... ሰዎችን በሙላታቸው በኩል አትመዝን፤ በየትኛው በኩል ሽንቁር እንዳላቸው አታውቅምና... በስንጥቃትህ አትሳቀቅ፣ የት ላይ መስራት እንዳለብህ አስታዋሽህ ነውና" ሲሉ መለሱለት...
___
ከጉድለትህ ጋር ግብግብ በፈጠርክበት ጊዜ ሳይቀር የሆነ አንድ ሰው የሙላት ተምሳሌት ልትሆን እንደምትችል አስብ... የሆነ ዓይነት ውበት፣ የሃሳብ ጥራት፣ ጥንካሬ እና ሰላም በጸጥታህ ውስጥ እንደተሸጎጠ ተመልከት...
ልብ በል...
ከምታስበው በላይ የተሟላህ፣ ከምታውቀው በላይ ክፍት ነህ... መንታ!! የምታተኩርበት ቦታ ዕይታህን ይወስነዋል...
___
@bridgethoughts
[የቀጠለ...]
🤔 ማብሰልሰያ - ፩
ሰይጣን አለ ብለን ብናስብና እንደተነገረን ክፋቱን ብንቀበል፣ maximum ሊያደርግብን የሚችለው ነገር ምንድነው?... ስቃይ ማብዛት?፣ መከራ መቆለል?፣ ለሞት መዳረግ? ወይስ ሌላ?... ታዲያ ሰይጣን የሚያደርገው እኛ እስካሁን ያላደረግነው ምን ነገር አለ?...
መንደሮችን አቃጥለናል... ሕፃናትን በቦምብ ደብድበናል... አፍላጋትን መርዘናል... ድንበር ፈጥረን ተቋስለናል... በረሃብ ሰው ፈጅተናል... ፍቅርን ሸቅጠናል... ሃቂቃን አፍነናል... ጨቅላ ሕፃን ደፍረናል... እርጉዝ ሴት በሳንጃ ዘንጥለናል... ሰውን በቁሙ አቃጥለናል... ስጋውን ቀርጥፈን ከርስ ሞልተናል... ከመሰዊያ ላይ አርደናል... በስልጣናችን ባልገናል... ዘርፈናል፣ ቀጥፈናል፣ ሰስነናል - ይህች ምድር በእኛ ምክንያት ያላየችው ምን ቀሪ መከራ አለ?...
[ለኢጎአችን እስከጠቀመ ድረስ ጆሮ አደንዛዡን፣ ዓይን አፍዛዡን ሁሉ አድርገናል - እስካሁን ካደረግነው የሚበልጥ ምንም ሌላ ነገር ወደፊት አናደርግም... ከኛ በላይ የሚያደርግ ሌላ 'ሰይጣንም' የለም]
🌟 "If Satan is the exile of love, then maybe redemption is not believing in God — but becoming someone who does not create hell for another."
እውነት ሰይጣን ካለ ግን በእርግጠኝነት በዚህ ሰዓት ጡረታ ወጥቷል... አልያም መዝገብ ይዞ ክፋታችንን እየከተበ ነው... ወይም ደግሞ ከከፋው ተግባራችን ልምድ እየቀሰመ ይሆናል...
ያን የ Desert father's wisdom ታስታውሱት የለ?...
በአንድ ገዳም ውስጥ፣ አንድ ወጣኒ መነኩሴ እንቁላል ይሰርቅና ተደብቆ ሲጠብስ ይገኛል...
'ምን እያደረግህ ነው?' ያገኙት አባት ይጠይቁታል...
'አይ አባ... ሰይጣን አስቶኝ...' ወጣቱ ይርበተበታል...
ጉዳዩን ከመስኮት በኩል ሆኖ ሲከታተል የነበረው 'ሰይጣን' ታዲያ እንዲህ ሲል ራሱን ነፃ አወጣ...
'አባ ውሸቱን ነው... ይህችን መላ ያለዛሬም አላየሁዋት'...
___
🌟 ጎበዝ ሰዋዊ ጉዳዮቻችን የሚመሩት በግላጭም በስውርም ነው... እኛ - አስበን፣ ወስነን የምንከውነው ብቻ አይደለንም... ከማለዳ ዕድሜያችን ጀምሮ በልቡሰ-ጥላ (subconscious mind) ሲሞላ የኖረው ፕሮግራምም በድብቅ ይመራናል፤ ይቆጣጠረናል...
እርሱ ማንነታችንን ይገነባል... እርሱ ግንኙነታችንን ይመራል...
እዚያ ቅይጥ መልካችን ይከተባል... እዚያ መሻት መጥላታችን ይቀመራል...
ደግነት ክፋታችን፣ ርህራሔ ተንኮላችን፣ ጨዋነት ወራዳነታችን፣ ንቃት ድንዛዜያችን የመንታ አንድ ሆኖ ይላቆጣል...
___
🤔 ማብሰልሰያ - ፪
ንድፈ ሃሳባዊውን መለኪያ ትተን በተግባር ብንፈተሽ 'ሰይጣን' ከሚባለው 'ትርክት' የሚለየን ምንድነው?...
ለምሳሌ - ሰይጣን 'ፈታኝ ነው' እንላለን... እኛም በአባይ ቃል፣ በአታላይ ጥቅም ሌሎችን በማማለል እንፈትናለን...
ሰይጣን 'ከፋፋይ ነው' እንላለን... እኛም 'ልዩነትን' የጥላቻ ምንጭ፣ 'ማንነትን' የጦር መስበቂያ ሰበብ አድርገን የሰውን ልጅ ስንበልት እንኖራለን...
ሰይጣን 'ሐሰተኛ ነው' እንላለን... ነግቶ እስኪመሽ ቅጥፈት፣ መሽቶ እስኪነጋ እብለት አሽሞንሙነን ወገናችንን እንወጋለን...
🦋 ሰይጣን ለመባል ቀንድ አያስፈልገንም - ከቀንድ በላይ የሚወጋ ምላስ አለን... ገሃነመ እሳት አያስፈልገንም - ከጥይት አረር እስከ ከፋው ኒውክለር ሁሉን ታጥቀናል...
___
አንድ ጥንታዊ የሱፊ ወግ ልንገራችሁ...
አንድ ቀን አንድ ደርቪሽ መምህሩን እንዲህ ሲል ጠየቀ...
"መምህር ሆይ፣ ሰይጣንን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?"
መምህሩ መለሱ...
"በቅድሚያ የእርሱን ጫማ መዋስ አቁም"
መምህሩ በጫማ ነጽሮት ውስጥ ውስጠ ቅኝታችንን ነው ያጠየቁት... አሳባቢ፣ ጥሩር ቀጥቃጭ፣ ኃላፊነት ካጂ ውስጠ ማንነታችንን...
ያመሰጠሩት ስለ ዓይነ ትልልቅ፣ ባለ ጨልጨሌ፣ ቀንዳም ሰይጣን ሳይሆን - ልናይ ስላልፈቀድነው ማንነታችን ነው...
___
Meister Eckhart እንዲህ ይላል...
“The devil is simply that which pushes you away from your own center.”
🌟 ማዕከል (center) የሰው ልጅ ለሕላዌው ጣዕም የሚፈጥርበት፣ እንዲሁም በመኖር ወጀብ ከመናወጥ የሚድንበት መልህቁ ነው... ፍቅሩ፣ አገልጋይነቱ፣ እሴቱ፣ የሕይወት ፍቺው... ሻገር ብሎ ደግሞ ከነፍስያው፣ ከምንጩ፣ ከምልዓተ ዓለሙ የሚዋደድበት እትብቱ... ከዚህ ማዕከል የሚገፋውን ነገር ነው ማላዩ ኤካርት 'devil' ሲል የጠራው...
___
መውጫ - መወጣጫ
___
🔔 [ሰይጣን ከአካላዊ ማንነት ይልቅ ከፍቅር የመፋታት ምልክት ቢሆንስ?... ምናልባትም የንቃት ስንጥቃት አልያም ከአማናዊው የማንነታችን ምንጭ የመለያያት ጥልቀት ቢሆንስ?...]
እንደ እውነቱ ከሆነ ክፉ አስፈፃሚ አይደለም ያለው - ፈፃሚው ራሱ እንጂ... በሌላ አነጋገር ወይ እኛ ሰይጣን ነን - አልያም ብቅ እልም የምትል ስይጥንና አለችብን...
___
👉 ጨለማን ሁልጊዜ ሻማ በመለኮስ አንፋታውም... አንዳንዴ ጨለማነቱን መቀበልም ይኖርብናል... በተለይ የውስጣችን ኑባሬ ሲሆን በዓይኖቻችን ልናየው መድፈርም ግድ ይሆናል... ልክ ራሳችንን በመስታወት ፊት እያየን እንደምናወራው ሁሉ - "አንተ - እኔን ነህ... ያልተፈቀርከው፣ ያልተጎበኘኸው፣ ያልተደመጥከው እኔ... አሁን አጠገብህ ነኝ፣ እያየሁህ ነው..." ልንለው ይገባል...
___
@bridgethoughts
.
.
.
ትናንት ስለመጣሽበት መንገድ አብዝተሽ ከተጨነቅሽ ዛሬን አልደረስሽም፤ ነገም ያንቺ አይደለም ማለት ነው...
የስብዕናሽ ጥራት የሚለካው ትናንት በፈጸምሻቸው ስህተቶች ሳይሆን ዛሬ ላትደግሚያቸው በምትይዥው አቋም ነው...
የእኔ እህት...
ከየት መምጣትሽ አይደለም ችግሩ ወደየት ለመሄድ መወሰንሽ እንጂ...
ወደኋላ የሚያዩ ዓይኖች ወደፊት የሚጓዙበትን መላ ሲቀምሩ - ተማሩ፤ ይበልጥ የሚቆዝሙበትን ትውስታ ሲጭሩ - ተቸነከሩ ይባላል...
መቸንከር ትፈልጊያለሽ?... [I know አትፈልጊም!!...]
የኔ ውድ!!...
ፊትሽን ከትናንት አዙሪ!... ሁላችንም እዚያ ነበርን... ደስ የሚል መልክ የለውም... ቢያንስ ሲሶ፣ እርቦ፣ ሩብ፣ ግማሽ፣ ምናምን ገጽታው ግርጣት አያጣውም...
የሚገርምሽ - ሊፈርዱብሽ፣ ሊያሸማቅቁሽ፣ ሊያሳንሱሽ የሚፈልጉ ሁሉ እዚያው ነበሩ... ማንም ንጹህ የለም!!...
ዛሬ ግን ውብ ነው!!... ከእጅሽ ያለ ዕንቁ - የምርጫ ጎተራ!!
ዳይ!!... ወደፊት ብቻ!!
____
@bridgethoughts
.
.
.
ድሃ ቤት ስታድግ 'ሃብታም' የማያውቃቸውን ብዙ ወጎች ትለምዳለህ...
ለምሳሌ...
እናትህ እራትህ ላይ ጨው በዛ አድርጋ የሰጠችህ ዕለት... ምግቡን ቀመስ ታደርግና...
'እማዬ፣ ጨው እኮ በዝቷል...' ስትላት፤
'አውቄያለሁ ዝም ብለህ ብላ... ውሃ እንዲያስጠጣህ ብዬ ነው' ትልሃለች...
___
የሆነ ቀን ደግሞ መባያው ያንስባታል... እንዲርብህ ግን በጭራሽ አትፈልግም ድስቱን ጠራርጋም ቢሆን ታቀርብልህና...
'በል እያጠቀስክ ብላ፣ መበያና ወንድም ማስፈራሪያ ነው' ትልሃለች...
___
ያው ሁሌ አይሳካም አይደል?... ሌላ ጊዜ ደግሞ ቤቱ ብጣሽ እንጀራ ብርቅ ይሆንበታል... ይሄኔ እናትህ...
'ይህችን ቀምሰህ ውሃ ጠጣበት፣ ሆድ እንዳሳዩት ነው' ብላ ለእራት ሽምብራ ቆሎ ትሰጥሃለች...
___
በዓል ደርሶ፣ ጎረቤት የተሰራው ሥጋ ወጥ ሲያስጎመዥህና ምራቅህን እያስዋጠ ሲያስቸግርህ...
'እማዬ፣ እዚህ ቤት ግን ሥጋ ወጥ የሚበላው መች ነው?' ስትላት...
'ያለለት... አለች የያለለት እናት፤ ያለለት ነዋ ልጄ!' ትልሃለች...
ምናልባት በጥያቄህ ገፍተህ ከተጫንካት ደግሞ፣ 'ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም' ብላ ኮስተር ትልብሃለች...
___
እናት ግን ሳታበላህ የማትበላ፣ 'አፈር ልብላ' ሳትልህ የማትውል፣ የሆዷን ጥያቄ በመቀነት ጨቁና የአንተን ሆድ ብቻ ለመሙላት የምትታትር... መሆኗን ልብ በል!!
___
ደግሞ ወዲህ...
ጥሬ ሽሮ ተበጥብጦ፣ ብትን ጨው በውሃ ሟሙቶ፣ ሚጥሚጣ ተጠቅሶ፣ በርበሬ ድልህ ሆኖ፣ ተልባ በውሃ ርሶ፣ ቃሪያ በጨው ተሰንጎ፣ ጎመን ተለብልቦ (ዘይት የጠፋ'ለት)፣ ሽንኩርት በጨው ተጠቅሶ... ወዘተ
በመበያነት የሚታወቁት ድሃ ቤት ብቻ ነው...
___
ሌላም አለ...
"አይቶ አጣ ቤት ጎመን የተቀቀለ ዕለት ሲጨበጨብ ያድራል"
"ሆድን በጎመን ቢደልሉት፣ ጉልበት በዳገት ይለግማል"
"ለአኩራፊ ምሳው እራቱ ነው"
"ምን ያመጣ ድሃ፣ ምን ያገሳ ውሃ"
"በሚያዝያ ጎመን የዘራ፣ ክረምቱን ሁሉ በላ"
"አህያ እንደምትታለብ፣ ከላሞች ፊት ትቅለበለብ"
"የችግር ክፉ እህል ማጣት፣ የኃጢዓት ክፉ ነፍስ ማጥፋት"
"ያፌን እስክውጥ ዕድሜ ይስጠኝ፣ ይላል እርኩም"
.
.
.
ዓይነቶቹን ተረት የምትሰማው ከድሃ ብቻ ነው...
___
Damn!!...
ዛሬም እዚያው ነን...
___
አንድ እውነት ግን አለ...
የድሃ ድህነት የሞራል አይደለም!!... ለማግኘት ብሎ ክብሩን አይጥልም!!!... ሆዱን ሊሞላ ሃገር አይሰርቅም!!!... ረሃብ ሊከላ ቃሉን አይበላም!!!...
___
@bridgethoughts
.
.
.
አንተ አለህ ከጎኔ - ዝናብ የታባቱ
ክንድህ ይከልለኝ - ጥላ ምኑ ብርቱ?
ገላዬ ቢርስም - በደመና ፍ*ራሽ
ምድጃ ነው ልቤ - በፍቅርህ ተለኳሽ።
___
@bridgethoughts
እንደማያስፈልገን እስኪገባን ድረስ የምንፈልገው ብዙ ነው።
___
@bridgethoughts
.
.
.
ፍጥነትን በምትሸልም ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው... እናም ሁሉም ነገር ይቸኩላል... ማሽኑ ይቸኩላል፣ እግረኛው ይቸኩላል፣ ንግግራችን ይቸኩላል፣ ማዕዳችን ይቸኩላል፣ ወዳጅነታችን ይቸኩላል፣ ጥላቻችን ይቸኩላል፣ ተግባራችን ይቸኩላል... የማይጣደፍ ነገር የለም...
እንቅስቃሴን ከለውጥ ሂደት ጋር እናምታታለን... ጫጫታን ከሃቂቃ ልክ እናዛንፋለን... ስክነትን ከጡዘት ጋር እናጋባለን... በንቃት ለመተንፈስ፣ ከልቡና ሆነን ለመስማት፣ ስሜታችንን ለማድመጥ በቂ ጊዜ የለንም...
[ይህ ምን ወለደ?... ጤናህን፣ ግንኙነትህን፣ ስሜትህን - አጢንና ምላሹን ለራስህ ስጥ...]
__
የተፈጥሮን ያልተነካካ ስርዓት (default setting) በመኖር ውስጥ ተጨማሪ ነገር ግድ አይደለም... አበቦች እንዲያብቡ 'ማሽነሪ' አይፈልጉም... ምድር ዙረቷን እንድትጠብቅ 'ሶፍትዌር' አትሻም... ጨረቃና ከዋክብት ለመድመቅ 'ካላንደር' አይጠይቁም... ወንዞች እንዲፈሱ 'ቱቦ' አያስፈልጋቸውም...
[እኔና አንተ ንቁ ሆነን ለመቆየት እንኳ ስንት ነገር ነው የሚያስፈልገን?...]
"Nature is pleased with simplicity. And nature is no dummy." — Isaac Newton
__
የዓለም ስርዓት ግለኝነትን ያበረታል፤ ተፈጥሮአዊነት ግን በሕብር ብቻ ይገለጣል... በጫካ ውስጥ አንዱም ፍጡር የብቻ ዓለም የለውም... ዛፎች የሚተነፍሱትን እንስሳቱ ይስቡታል፣ የአራዊቱ ውጋጅ ምድርን ያለሰልሳል... በተፈጥሮ ውስጥ ቅርጹን የሚቀይር እንጂ የሚጠፋ ነገር የለም...
ባልተረዳነው ጊዜ እንኳ የሚሰራ፣ ልንተማመንበት የሚገባ ታላቅ አስተውሎት ተፈጥሮ ውስጥ አለ... የኛን ቁጥጥር የማይፈልግ፣ ሁሉን በሰዓቱ የሚከውን፣ በፍጽምና የሚጓዝ አስደማሚ ጥበብ ተፈጥሮ ውስጥ አለ...
የምታዋጣው ክህሎት ሳይኖር የደም ዝውውርህ ይሳለጣል፣ ልብ በማትለው ጊዜም ቢሆን ትንፋሽህ ገብቶ ይወጣል፣ የሰውነትህ ክፍሎች (ልብህ፣ ኩላሊትህ፣ ጉበትህ...) ከአንተ ቁጥጥር ውጪ ሆነው መደበኛ ተግባራቸውን ይከውናሉ...
“Look deep into nature, and then you will understand everything better.” — Albert Einstein
ተፈጥሮ ውስጥ እያከማቹ መዝለቅ የለም፣ እየተው መሄድ እንጂ... ዛፎች ቅጠላቸውን ያረግፋሉ - በስብሰው ምድርን ያለማሉ፣ ፍሬያቸውን ይጥላሉ - ሌላ ዘር ይተካሉ፣ ብስሉን ይሰጣሉ - ረሃብ ይከላሉ... ደመና ይዘንባል፣ ከዋክብት ይወድቃሉ፣ ምድር ከፈኗን ትጥላለች...
[እኔና አንተስ?... ትርፋችንንም አንጋራም!... ይሄ ምን ወለደ?...]
___
ተፈጥሮ በውድድር ስርዓት እርስ በእርስ አትባላም - ሚዛን አኑራ ትጓዛለች እንጂ... መስመር አስምራ ድንበር ገፉብኝ አትልም - ልዩነት አጥፍታ ታጣምራለች እንጂ...
ተፈጥሮአዊነት ኋላ-ቀርነት አይደለም፣ አሁንና እዚህ መገኘት ብቻ እንጂ... ስልጣኔዎቻችንን መናቅ አይደለም፣ ጌቶቻችን እንዲሆኑ አለመፍቀድ እንጂ... ኑረትን ማጣጣል አይደለም፣ አማናዊውን ማንነት አለመርሳት እንጂ...
ነገሩ እኮ መመለስ ነው... ፊትን ወደ ቤት ማዞር!!... ወደ ጥንተ ማንነታችን መጓዝ...
____
አስተውለህ ካየህ...
በስልጣኔ ስም ኑረትን አወሳስበናታል... በውድድር ስም ዓለሚቱን ሲዖል አድርገናታል... ሃብት በማካበት ስም ንፍገትን አንብረናል... ምድሪቱ የገጠሙዋትን ፈተናዎች በሙሉ ብትመረምር የሰው ልጅ የተፈጥሮን ስርዓት ትቶ 'የኔ' የሚለውን ዘዬ በመከተሉ ምክንያት የገባበት ጭንቅ ጎልቶ ይታይሃል...
ጦርነት፣ ረሃብ፣ ስደት፣ እርዛት፣ አምባገነንነት፣ ጭካኔ፣ ጥላቻ... የሁሉም ምንጭ እኛው ነን... ችግሩ ያለው የፈጠርነው የዓለም ስርዓት ላይ እንጂ የተፈጥሮ 'ኢፍትሐዊነት' ላይ አይደለም...
ወደ ቤታችን እንመለስ... የተፈጥሮን default setting እንኑር...
___
ይህ ከዓለም ክፋት የመመነን ጥሪ አይደለም... በውስጧ ሆኖ የመንቃት ደወል እንጂ... ጨለምተኝነት፣ ኢ-ዘመናዊነት፣ አልያም የለውጥን ተፈጥሮአዊነት የመካድ ጉዳይ አይደለም... የእርጋታ፣ የመጠየቅ፣ ትንፋሽ የመውሰድ፣ የተማሩትን ትቶ ከተፈጥሮ ስልተ ምት ጋር የመጣማት ፍንጭ እንጂ...
[በግዳጅ ውስጥ የመኖር ጭቆና ሳይሆን በፍቃድ የመፍሰስ ሕልውና ነው... በፍርሃት የመጓዝ ድንብርብር ሳይሆን በነፃነት ከፍ የማለት ግብር ነው...]
ይህ የምልሰት ግብዣ ነው... አዲስ ነገር የመሆን ሳይሆን ወደ ቦታ የመመለስ ጥሪ... ስር የመትከል፣ መሬት የመርገጥ፣ የመስከን ደወል...
___
@bridgethoughts
እዚህ መንደራችን ውስጥ @HiwotWog ቻናል ላይ አጫጭር ታሪኮች ስትከትብ የምታውቋት ደራሲት ሕይወት እምሻው:
'ነገ ከስራ በኋላ አብራችሁኝ ብትሆኑ:
ቡና ፉት እያላችሁ፣
ወግ እየጠረቃችሁ
ጮርናቄ እየገመጣችሁ
፭ መፃሕፍት ሸምታችሁ ትደሰታላችሁ' ብላችኋለች...
___
ቦታ - አራት ኪሎ [ኢክላስ ሕንፃ - ዋልያ መፃሕፍት መደብር]
ሰዓት - ማምሻ 11:00
የመግቢያ ዋጋ - ምንም አይጠየቁም፣ ይልቅ ለመገኘትዎ ዋጋ ይቀበላሉ።
___
/channel/HiwotWog
“Think of Others”
__
As you prepare your breakfast — think of others.
Don’t forget to feed the pigeons.
As you conduct your wars — think of others.
Don’t forget those who want peace.
As you pay your water bill — think of others.
Think of those who have only the clouds to drink from.
As you go home, your own home — think of others — don’t forget those who live in tents.
As you sleep and count the stars, think of others — there are people who have no place to sleep.
As you liberate yourself with metaphors think of others — those who have lost their right to speak.
And as you think of distant others — think of yourself and say‘I wish I were a candle.
___
By: Mahmoud Darwish
___
[Mahmoud Darwish (1941–2008) was a Palestinian poet, essayist, and one of the most celebrated literary voices of the Arab world. He’s often called the poet of exile, the voice of Palestine, and a modern mystic of resistance and longing.]
___
@bridgethoughts
.
.
.
ከፊትለፊቴ ነው፣ ፍሬን የበጠሰ መኪና ድንገት የነጠቀው... ማንም ቦታው ላይ አልነበረም... ሮጬ ሄድኩ... ሆኖም በደም የጨቀየ ሰውነቱን ልነካ አልደፈርኩም... እጆቼ ተንቀጠቀጡብኝ... ደግሞስ ምን አደርግለታለሁ?...
በሰከንዶች ውስጥ ዕልፍ ነገሮች ተለዋውጠዋል...
ልብሶቹ አጥንት፣ ስጋና ደም ተላቁጠውበታል... ፊቱ እሳት ያገኘው ፕላስቲክ መስሏል... የሰውነት ክፍሎቹ ተሰባብረው ደቀዋል...
ዓይኖቹ ሊያወሩኝ እንደሚፈልጉ ነገሩኝ... መንቀሳቀስ አይችልም... ዝቅ አልኩ፣ አፉን የሞላው ደም ቱግ እንደሚል ጀበና እያስቸገረው አጉተመተመ... የምጥ ያህል በከበደ ትግል ውስጥ ሆኖ ደጋግሞ የነገረኝን ገጣጥሜ ልሰማው ሞከርኩ...
"ለልጄ እያየሁህ ነው በለው" ነበር ያለኝ...
ትንፋሹ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀጥ አለች...
ይህን እንዲለኝ ነበር ነፍሱ የጠበቀችው?...
የማላውቀውን ሰው መልዕክት ተሸክሜ የማላውቀው ልጁን በሕሊናዬ አመላለስኩ... በአካል ኑረት አብሮት ባይዘልቅ በመንፈስ ጎዳናው እጁን ይዞት እንዳለ እንዲሰማው ፈልጓል...
በዚህች የቅጽበት ዕድሜ፣ በአስደንጋጭ ክስተት ውስጥ፣ ምንም መሆን በማይችልበት ሁኔታ፣ 'ልጄ' የማለትን አቅምና ትውስታ እንዴት አገኘ?... ነፍሱ በምን ፍጥነት የስጋ ሞቱን ነገረችው?...
ውስጤ ብዙ ጥያቄዎች ተመላለሱ... ፈዝዤ ሳለሁ አካባቢው በጩኸት ተናጠ... እንደመንቃት አልኩ... ሰዎች ከበቡን... ልራመድ ስሞክር ግን እግሮቼ ጠፉብኝ... ደንዝዘው ነበር...
"ለልጄ እያየሁህ ነው በለው"
ልረሳ በማልችለው ፊት፣ ሊረሳ በማይችል ቃል፣ ቀድሞ ዕውቂያ የሌለን ሰው በልቤ ሰሌዳ ላይ ላይጠፋ እንደተከተበ ገባኝ...
____
[Re-ለአባቶች ቀን]
___
@bridgethoughts
.
.
.
በሰዎች አዕምሮ ውስጥ መንጎዳጎድ ደስ ይለኛል... በተለየ ሁኔታ ቀልቤን የሚስብ ሰው ሳገኝ 'ምን እያሰበ ይሆን?' ማለት አዘወትራለሁ...
___
'ወክ' እያደረግሁ ነው...
አሁን ለምሳሌ ይሄ ከፊቴ እያለፈ ያለው ሰውዬ ከሰው ጋር እያወራ እንዳለ ሁሉ እጁን እንዲህ የሚያወናጭፈው ምን እያሰበ ነው?... ተመልካች ጉድ እስኪለው፣ ለራሱ እንኳ እስኪገርመው 'ለብቻው' ሚያወጋው ምን ገጥሞት ነው?... ጎጆው ስንት ቀዳዳ ቢከፍትበት - ወገንስ ምን ያህል ቢከፋበት ይሆን?...
የተዋት ሚስቱ ናት የተወችው ኑረት እንዲህ 'ምታወራጨው?... የአለቃው ንግግር ብስጭት ነው፣ የበደለው ጎረቤቱ ቁጭት አቅሉን ያቀጨጨው?...
ከቶ ራሱን እንዳይቆጣጠር ያደረገው ምንድነው?... ልማድ ወይስ ጉድለት?... ህመም ወይስ ጭንቀት?...
___
ከባሻገር...
እኒያን ጥንዶች እንዲህ ያወሻሸቃቸው ምንድነው?... የፍቅር ቀለበት ወይስ የስሜት ዘለበት?... የዕድሜ ልክ ፈፋ ወይስ የወራት አረፋ?...
እንግዳ ደራሽ ቢጠይቅ ምንና ምን ነን ይላሉ?... መውደድ ያቆራኘን ጥንዶች ወይስ መንገድ ያገናኘን ቧልቶች?...
እርሷ ዓይኖቹን ስታይ የምታስበው ምንድነው?... እርሱ ጉንጯን ሲስም የሚያልመው መቼን ነው?... የጋራ ነገ አላቸው?... እርሷ በነፍሱ ዘንድ ቦታዋ ምንድነው?... እርሱ በእቅፏ ውስጥ ጥጋቱ ወዴት ናት?... በሕይወቱ ውስጥ ሹፌር ናት ተሳፋሪ?... ለዕለታቶቿ አባሪ ነው ኗሪ?...
___
ያ የጎዳና ተዳዳሪ ልጅ ምንድነው የሚያስበው?... ይህን ቤንዚን ሲስብ ምንድነው 'ሚሰማው?... ብርድ ይረሳበታል ወይስ ሆድ ይሸነግልበታል?... ቀኑን ያሳልፍበታል ወይስ ራሱ ያልፍበታል?...
በአባት የታቀፈ ልጅ ከአጠገቡ ሲያልፍ ምን ይሰማዋል?... በእናት ስስት የተጌጠ ህፃን ምን ያስታውሰዋል?...
___
እኒያ ከበተስኪያን ደጅ የቆሙ እናት ምን እየለመኑ ይሆን?... ከሚጨናበሱ ዓይኖቻቸው፣ ማድያት ካጠቆረው ፊታቸው ዘንድ ተስፋ ምንድን ናት?...
ፈንጠር ብላ የምታነባዋ ወጣት ሴት መሻቷ ምን ይሆን?... ከገረገራው ያቆማት፣ ዓይኗን በእንባ ያጠባት ምን ሊሆን ይችላል?...
ጉንጯን እየሰረሰረ የሚወርደውን የእንባ ጎርፍ የትኛው ሃዘኗ ፈጠረው?... የሚንሰቀሰቅ ሰውነቷንስ በደል ማን ጨክኖ ወለደው?... የባሌን ልብ መልስልኝ ይሆን የምትለው?... ይህን ፈተና ከኔ አርቀው ይሆን የምትለው?... መውጫውን አሳየኝ ይሆን 'ምትለው?... ምንድነው የሆነችው?...
___
ያቺ ስልክ እንጨት ተደግፋ የቆመች ሴተኛ አዳሪ ስለ ለሊቷ ምን እያሰበች ይሆን?... ዛሬስ 'ሚተኛት ምን ዓይነቱ ነው?... ጨካኝ ነው አዛኝ?... ማጋጭ ነው ባካኝ?... በልቧ የሚመላለሰው ጸሎት ምን ይሆን?... 'ከማላውቀው ሰው የማይታወቅ ዓመል፣ ከሚያውቀኝ ሰው የወሬ ደለል - ከልለኝ' ይሆን የምትል?...
ባለትዳሮች ምን ምን ይሏታል?... 'ሚንቃት ስታይ ምኗን ያንቃታል?...
___
.
.
.
እርሱ ምን እያሰበ ይሆን?...
.
.
.
እርሷስ ምን እያሰበች ይሆን?...
___
ከሰው ልጅ የአረማመዱ ቅኝት፣ ከአዋዋል ከአነጋገሩ ስምረት፣ ከኑሮ ከጎጆ ታዛው፣ ከልብሱ ከከፈን ደብዛው - ባሻገር...
ብዙ ተረክ ብዙ ታሪክ አለ...
ብዙ ሃዘን ብዙ ስብራት አለ...
ብዙ ቁስል ብዙ ህመም አለ...
በሆድ ይፍጀው የታዘለ...
አሁን አንቺ ምን እያሰብሽ ነው?...
___
@bridgethoughts
.
.
.
ቅድሚያ የሰጠኸው ሰው - ከፊትህ አክብሮትን ሳይሆን ፍርሃትን ካነበበ፣
አደራ የሰጠኸው ሰው - የልብህን ማመን ሳይሆን የድርጊትህን ሞኝነት ካሰበ፣
ሙሉ ጊዜህን የሰጠኸው ሰው - ፍቅርህ ሳይሆን ስራፈትነትህ ከተሰማው፣
ገንዘብህን የሰጠኸው ሰው - ችሮታህን ረስቶ መጠኑ አንሶ ከታየው፣
የረሳህለት ሰው - ይቅር እንዳልከው ሳይሆን እንዳልተሰማህ ካመነ፣
ያገለገልከው ሰው - እርዳታህን ትቶ ግዴታህን ብቻ ካሰበ፣
ከበላይህ ያለ ሰው - የሃሳብህን ፋይዳ ከቆምክበት መደብ ካለካካ፣
የእጅህን ንጽህና የሚያውቅ - ዕድል ስላላገኘህ እንጂ መስረቅ ስላልፈለክ አይደለም ብሎ ካሰበ፣
ቆርሰህ ያካፈልከው - የሰጠኸውን ሳይሆን ከእጅህ የቀረውን ካስተዋለ፣
ግማሽ መንገድ የሄድክለት - ከጠበቀህ በቆመበት፣
ለወፌ ቆመች ተለጉሞ - ይድፋህ ለማለት ካደረ ቆሞ፣
እንዲለወጥ እጅ ያላቀበለ - ለትችት ከተቀባበለ፣
ባወቅሁሽ ናቅሁሽ ያንተን ጡብ ንቆ - የሩቅ መናኛ ካየህ አድንቆ፣
.
.
.
ወዳጄ ችግር አለ...
___
@bridgethoughts
ሞባይሉን ጆሮው ላይ ደቅኖ ከስልኩ ወዲያ ጫፍ ያለውን የድምጽ ምንጭ ይቀዳል...
ስልክ ያልያዘበት እጁ እንደ ጉድ እየደነሰ ነው... ጥርሶቹ አፉ ጠቧቸው ከከንፈሩ ጋር ትግል ገብተዋል... ዓይኖቹ ፍትት ብለው ይስቃሉ... የፊቱ ፍካት አንድ ከተማ ያበራል...
ዓይኖቼን ከእርሱ መንቀል አልቻልኩም... ልጁ የሆነ የሚጋባ መንፈስ አለው...
የሁኔታውን ሰበዝ በስልኩ ሞገድ በኩል ዘርግቼ ከወዲያ ጫፍ ያለውን የደስታ ምንጭ ማንነት ለመገመት ሞከርኩ...
መጠራጠር አልፈለግሁም...
እንዲህ ወደ እንቦቃቅላ ዘመን መልሶ ለማፍነከነክ ከእርስዋ ውጪ ማን ተጠያቂ ሊሆን ይችላል?...
እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አድርጎን ነበራ...
___
@bridgethoughts
.
.
.
'የኔ ሁኚ' የማልልሽ የኔ በመሆን የምታጭው [የሚመስለኝን] ሁሉ ስለማስብ ነው... አብሮነትን የማልጠይቅሽ ማግስት የሚነጥቅሽ [የሚመስለኝን] ሁሉ እያብሰለሰልኩ ነው...
(የሚመስለኝ ያልኩሽ - በእኔ ልብ ውስጥ ያለውን እምነት እንጂ አንቺ ዘንድ ያለውን ጥንካሬ ስለማላውቅ ነው...)
ከልቤ እልፍኝ ያልጋበዝኩሽ ስለማልፈቅድሽ አይደለም... መንገዴን ያላጋራሁሽ ስለማልወድሽ አይደለም... ይልቁን ስለምጠነቀቅልሽ ነው... [የኔ በመሆን የምትከፍይው ዋጋ እንዳይኖር በመስጋት... ወይም በጥሬ ቃል 'ደስታዋን ስለ አብሮነታችን ሰውታ ብታዝንብኝስ?' ብዬ በመፍራት...]
[እንግዳ ነገር ይመስላል አይደል?... 'የነገን እግዜር ያውቃል' በሚል ተስፈኛ ሕዝብ መሐል በቅሎ 'ነገ ብትከፋብኝስ?' ብሎ ማሰብ ይገርማል አይደል?...]
____
[የነግ ፍርሃት እያጠየመብኝ እንጂ እኮ...]
ልብሽ ለኔ ያላትን ቦታ እረዳለሁ - [ልብሽን እንዳልሰብራት ደግሞ እፈራለሁ...]
ስታገኚኝ የፊትሽ ጸዳል ለልቤ እንዲያበራ አውቃለሁ - [የኔ አድርጌሽ ሳቅሽን እንዳልነጥቅሽ እያልኩ ግን እፈራለሁ...]
ጨዋታሽ ደዌ ሲፈውስ፣ ቃላትሽ ለነፍስ ሲደርስ፣ ፈገግታሽ መንፈስ ሲያድስ አውቃለሁ - [አብሮነታችን ስሜትሽን እንዳያጎሸው ግን ሁሌም እሰጋለሁ...]
[ግን ደግሞ ሰው አይደለሁ?...]
ዛሬ የገባኝ ሁሉ ከነፃነትሽ ላለመወለዱ፣ ዛሬ የወደድኩት ሁሉ ነገም ለመራመዱ እርግጠኝነት እንዲከበኝ እሻለሁ...
[እናም በልቤ እጠይቅሻለሁ...]
የመጣሁበት መንገድ አያዝልሽም?... የምደርስበት ነገ አያስከፋሽም?... እርጅናዬ ውስጥ ልትኖሪ ትሺያለሽ?... በጉዞዬ ልታብሪኝ በቂ አቅም አለሽ?... [ይኸውልሽ ማሬ፣ ፊቴ ላይ የማታነቢው ምሬት ከውስጤ ሊኖር ይችላል...]
ውድቀቴ ተስፋ አያስቆርጥሽም?... ድህነቴ አያስፈራሽም?... ቀርነቴስ አያሳቅቅሽም?... [ከዘመነኞችሽ ጋር ያለኝን መልከ ብዙ ልዩነትና ርቀት አውቀዋለሁ...]
ፍቅሬ ይበቃሻል?... ቤቴስ ይስብሻል?...
ህመሜን አትጠየፊውም?... ድካሜንስ አትሰቀቂውም?...
[ይሄ ሁሉ ይቅር...]
ስለ ውሳኔሽ አትጸጸቺም???...
___
ጣፋጯ...
ለነዚህ ጥያቄዎች የአዎንታ ልብ ከሌለሽ 'ና' አትበይኝ... እኔም 'ምጪልኝ' ብዬ አላስጨንቅሽም...
የወደድኩሽ የማትፈልጊውን እንድትኖሪ ከመጨከን ጋር ስላልሆነ ምርጫሽን አከብራለሁ... ግን አትርሺ - ስላላበርን ፍቅሬ ፈጽሞ አይቀየርም...
___
ይህን ግን ለምን ፃፍኩልሽ?...
ራስ ወዳድ እንዳልሆንኩ እንድታውቂ ይሆናል... [ምናልባት ደግሞ ነፃነትሽን ላስታውስሽ ብዬም ይሆናል...]
[አየሽ... ሰው በገዛ ልቡ ውስጥ ስላለች የፍቅር ኩራዝ እንጂ በሌላኛው ሰው ልብ ውስጥ ስለተዘጋጀለት እቶን መውደድ በቀላሉ እርግጠኝነት አይሰማውም... በመኖር ካልፈተነው በቀር...]
ሁሌም ግን እወድሻለሁ 💞
___
@bridgethoughts
.
.
.
... የሰው ልጅ 'ሰውነት' የተለየው በጥላው ቅርጽ አይደለም... በሚጠራበት ስም፣ በተሸከመው ስመ-ማሕተም፣ በሰበሰበው ሃብት እና ምድራዊ ቁሳቁስ አይደለም... በልቡ መሰዊያ ላይ በሚያቀርባት የዕጣን ሽቱ፣ ዓይን ባላየው ጊዜ በሚንበረከክላት እውነቱ፣ ሁሉ ባወገዘው ጊዜ በሚቆምላት እምነቱ እንጂ...
___
@bridgethoughts
.
.
.
እንዳልነበርክ ለመሆን ሰከንዶች እንኳ ረጅም ናቸው... አትታበይ!!
___
@bridgethoughts
ማስተንከሪያ
___
📢 Are we evolving or are we just getting better at masking our madness?
[በጥያቄ ነቃሁ... ጠዋቴ ከማወቅ ጉጉቴ ጋር በራች... እንዲሁ ነኝ... አንዳንድ ቀኔን የሚረከቡ ሃሳቦች ማለዳዬ ላይ ይራወጣሉ... ዛሬም የሆነው እንዲሁ ነበር...]
እናም ጠየቅሁ...
'እውን ሰይጣን ይሉት 'አካል' አለ?... ቀንዳም፣ የጨለማ ገዢ፣ አስፈሪ፣ ጨካኝ entity በሕዋችን ላይ ታቅፏል?... ወይስ ላልተቀበልነው ተፈጥሮአችን፣ ለውድመት፣ ለበደል፣ ለግፊያችን - ማምለጫ፣ ማቋረጫ፣ መሿለኪያ የተቀመጠ የስርየት ፍየል ይሆን?... 🤔🤔🤔
___
ማጮለቂያ... 👀
___
ርዕዮት - ፩
የሐይማኖት መጽሐፍት የሰይጣንን ኑባሬ ይቀበላሉ... ለምሳሌ ክርስትና 'የተጣለው መልዓክ፣ መከራ አማጭ፣ ፈታኝ' ብሎ የሚጠራው ሰይጣንን 'ከመለኮት ትዕዛዝ በተቃርኖ የሚጓዝ አማጺ' አድርጎ ያስቀምጠዋል...
በእስልምና 'ኢብሊስ' ተብሎ የሚጠራው ሰይጣን 'ለአዳም ባለመገዛቱ የተባረረ፣ የኩራትና ያለመታዘዝ ምልክት ነው'...
አይሁዶች በዕብራይስጥ 'ሃ-ሴታን' ወይም ከሳሽ ሲሉ የሚጠሩት ሰይጣን 'በፈጣሪ የፍርድ ችሎት ላይ የሚቀመጥና የሰዎችን ታማኝነት የሚፈታተን ነው' ሲሉ ያስተምራሉ...
ርዕዮት - ፪
ነገሩን ምዕራባዊ መሰረት ካላቸው ሐይማኖቶች አስተምህሮ አውጥተን በአሳቢያን እና ማላዮች መነጽር ብንመለከተው ሰይጣን ከአካላዊ ግዝፈት ይልቅ ምልክታዊ ጉላት ያይልበታል...
ሰይጣን የሰው ልጅ ባሕሪያዊ ጽላሎት (Inner shadow) ትዕምርት ሲሆን ያልተፈተነ ፍርሐት፣ ስግብግብነትና ድብቅ ጭካኔያችን ነጸብራቅ ነው...
ከእውነት፣ ከፍቅር እና ከሕላዌ ነቅዕ (Being) የመለያየት ተምሳሌት፤ እንዲሁም ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን ለማምለጥ የምንከለልበት ዓይነ-ርግብ (mask) ነው...
Carl Jung ቆንጆ አድርጎ እንዳስቀመጠው...
🔔 "The devil is the personification of the shadow side of human nature." 🔔
ማላዮችም ስለ ሰይጣን አብዝተው ከመናገር ይልቅ ስለ ንቃትና ተገንዝቦት ማውጋትን የሚመርጡት ለዚህ ነው...
ለምሳሌ ሱፊስቶች - “There is no Satan but the ego unobserved.” በማለት ከነዩንግ እሳቤ ጋር ሲዛመዱ ሌሎች ምስራቃዊ መሰረት ያላቸው አስተምህሮዎችም ከዚህ መሰረት ብዙም ያልራቀ ዕይታን ያስተጋባሉ...
___
📌 የሰይጣንን እሳቤ የወለደው ክህደት፣ ድንዛዜ እና ኃላፊነትን ያለመውሰድ ቅዋሜ ነው... ሁሌም ቢሆን አጥፊነታችንን መቀበል ሲቸግረን ሌላ ተወቃሽ እናሻትታለን... የሁኔታው ሰበብና የቅጣቱ ተቀባይ እኛው ራሳችን ብንሆንም እኛን ተገብቶ እንዲጠየቅልን የምንፈልገው የጦስ ዶሮ መፈለጋችን የተለመደ ነው...
📌 ክፋታችንን ውጫዊ ስናደርግ 'ለምንድነው ይህን ያደረግሁት? የትኛው እኔታዬ ነው ይህ እንዲሆን የፈለገው?' ብለን ከመጠየቅ ይልቅ 'እኔ አላደረግሁትም ወይም ሰይጣን አስቶኝ ነው' የማለትን ቀላል መንገድ እንመርጣለን...
___
@bridgethoughts
.
.
.
ለራስህ እውነተኛ ስሜት ታማኝ ሆነህ ትቆያለህ ወይስ ለሌሎች ስሜት ለመመቸት ስትል ሚዛን ትስታለህ?
ዋጋ የምትሰጣቸው ነገሮች ምንነት አጠቃላይ ነገርህን ይወስኑታል... እሴትህ ወይም 'value' የምታደርጋቸው ነገሮች ስላንተ ያለውን አጠቃላይ እውነት ይናገራሉ...
ለሃቅ ዋጋ ትሰጣለህ - እውነተኛ ትሆናለህ... ሃሰት ካልጎረበጠህ በክህደት ትሰለጥናለህ... ገንዘብ ታመልካለህ - ለሃብት ስትል እስከ መግደል ትደርሳለህ... ባለህ ከተብቃቃህ መካፈል ታውቃለህ...
የሰው ልጅ 'ሰውነት' የተለየው በጥላው ቅርጽ አይደለም... በሚጠራበት ስም፣ በተሸከመው ስመ-ማሕተም፣ በሰበሰበው ሃብት እና ምድራዊ ቁሳቁስ አይደለም... በልቡ መሰዊያ ላይ በሚያቀርባት የዕጣን ሽቱ፣ ዓይን ባላየው ጊዜ በሚንበረከክላት እውነቱ፣ ሁሉ ባወገዘው ጊዜ በሚቆምላት እምነቱ እንጂ...
ብዙዎች 'ለወርቅ' ይሰግዳሉ - ጥቂቶች የጸጥታን ውበት ያመልካሉ... እልፎች እውነትን ለጭብጨባና ርካሽ አድናቆት አሳልፈው ይሰጣሉ - ጥቂቶች የሃቂቃቸውን ላምባ ከፍ አድርገው ይጓዛሉ...
እነዚያ 'እኛን ምሰል' ማለት ያዘወትራሉ - ያልመሰለን ማራቅ፣ ያልመሰለን ማድቀቅ ያውቁበታል...
እነዚህ መሆንን ይኖራሉ - መምሰል የነፍስያን ቀለም የሚያጠፋ ጥላት፣ ውስጠትን የሚበላ ሻህላ እንደሆነ ያውቃሉ...
አዎን... መንጋውን ከሚያብር ፍም ይልቅ በሚያረግድ ንፋስ ፊት የሚቆም የኩራዝ ነበልባል የበለጠ የሞራል ብርታት አለው...
እሴተኝነት እስረኝነት አይደለም - ፍሬ እንጂ... አጥልቀህ ስትቀብረው ተልቆ ብቅ ይላል... ሥጋህ እንኳ ቢያልፍ ለስምህ ዘብነት ደን ሆኖ ይበቅላል... ልጆችህ ይኮሩበታል - መንዝረው ይከብሩበታል...
ይህን ያጣህ'ለት ግን ማንም ትሆናለህ... ከቆምክበት ሞገስ አይኖርህም... ባለፍክበት ክብር አይቆይልህም...
እንጂማ...
ሰው ከእሴቱ ውጭ ምንድነው?...
___
@bridgethoughts
.
.
.
የምሰራበት ተቋም "በቀጣይ አገልግሎቶቼን የማቀርበው የፋይዳ መታወቂያ ላላቸው ሰራተኞች ብቻ ስለሆነ ከወዲሁ መታወቂያ እንድታወጡ" የሚለውን ማሳሰቢያ ሰብሰብ ብለን በተቀመጥን ባልደረቦች የእጅ ስልክ ላይ ላከ...
ስልኮቻችን ጢው፣ ጺው፣ ኳኳ፣ ቡምቡም... እያሉ 'እንደየሃገራቸው' ጮሁ...
ይህ እንደሆነ አንደኛው ባልደረባችን 'ቴክስቱን' አንብቦ ሲጨርስ ለሌላኛው "እከሌ ፋይዳ አለህ?" ሲል ጠየቀው...
Oh my day!!
ሃሳቡ እኮ ገብቶኛል... ግን ደነገጥኩ...
ወደ ራሴ ዞሬ እኔዬን ጠየቅሁት... "እውን ፋይዳ አለህ?" ብዬ...
ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት ጥያቄ ለመመለስ ሲያምጥ ያላየሁት እኔታዬ ቁዘማ ሲወርሰው ታዘብኩ...
ፋይዳ አለህ?... ፋይዳ አላችሁ?...
በቤታችሁ፣
በሰፈራችሁ፣
በማሕበረሰብ፣
በሃገራችሁ፣
በሕይወታችሁ፣
በመኖራችሁ፣
በስራ ቦታችሁ... ፋይዳ አላችሁ?... እውነት ፋይዳችሁ ምንድነው?...
የመኖር ዘፍጥረት፣ የሕላዌ አሃዱ፣ የመውጣት መግባታችን ውበት ፋይዳ ነው... አበርክቶ... ዋጋ... ክብረት... ከተቀበሉት በላይ መስጠት፣ ማኖር፣ መብራት፣ መምራት፣ ወዝ መቀላቀል፣ መፍጋት፣ ምርኩዝ መሆን...
እንጂማ መኖር ምን ትርጉም አለው? - እየፈየዱ ትርጉም ካልሰጡት...
___
ፋይዳ አለህ?... ፋይዳ አለሽሽ?...
___
ሁለቱ የምድራችን ታላላቅ ነፍሶች ስለ ፋይዳ ይህን ብለው ነበር...
"Only a life lived for others is a life worthwhile." ~ Albert Eisenstein
"The best way to find yourself is to lose yourself in the service of others." ~ Mahatma Gandhi
___
@bridgethoughts
ፈሪ የሚያስፈራራህ ራሱ በሚፈራበት መንገድ ነው።
___
@bridgethoughts
"... Part of me was frustrated because what did i do wrong?
Because you heard the music when i wrote the song."
___
Celia
___
@bridgethoughts
.
.
.
Default setting
___
ከሃሳብ የሚያረጅ ስልተ-ምት አለ... ከቋንቋ የሚጠልቅ ጸጥታ አለ... በጎህ መቅደድ እርጋታ፣ በምትወድቅ ቅጠል ዥውታ፣ በሚመላለስ ትንፋሽ ፋታ፣ አንድ ስም የለሽ መሆንታ (being) አለ... ተፈጥሮአዊነት!!... ከስርዓቷ ጋር መዛነቅ፣ ከቅኝቷ ጋር መስማማት፣ ከአደራረጓ ጋር ስሙር መሆን...
የሆነ ጊዜ ከዚህ ተፈጥሮአዊ ቅንብር (setting) ጋር ያለ ድካም ሕብር እንፈጥር ነበር... ሰዓታት ከመተለማቸው በፊት፣ ጫጫታ ከመንገሱ በፊት፣ የሆነ ሰው ለመሆን ከመራወጣችን በፊት... ከኑረት ጡዘት፣ ከውድድር ቅኝት፣ ከፉክክር ውጥረታችን በፊት ከተፈጥሮ ስልተ-ምት ጋር ተጣጥሞሽ ነበረን...
ዛሬ ይሄ የለም...
ራሳችንን ዕረፍት አልባ አድርገነዋል... መንፈሳችንን በታትነነዋል... ለነፍሳችን ዓለም ባዕድ ሆነናል... የፈጠርነው ስርዓት ከተፈጥሮ ዝማሜ ለይቶን ሳይበቃው ስጋችንን እያጎሳቆለ ነው... ግንኙነታችንን እያቀጨጨ ነው...
የምር... ነፍሳችን ታፍናለች...
የሆነ ዓይነት መደንዘዝ ውስጥ እንዳለን ብናውቅም ስህተት ነው ለማለት ወኔ አላገኘንም... አንዳች መርግ ቢጫነንም መጉበጣችንን መቀበል አንፈልግም... የተፈጥሮን ስልተ-ምት ንቀን የፈጠርናቸው ሁሉም ስርዓቶች መልሰው እየበሉን ነው... ሆኖም በስሪታቸው ጥመት ላይ ስላልተግባባን በፈጠሩብን መዓት ላይ የጋራ አቋም አልያዝንም...
በቤትህ፣ በሰፈርህ፣ በከተማህ፣ በሃገርህ፣ በዓለም ዙሪያና በምድሪቱ ሁሉ ምን እየሆነ እንዳለ ተመልከት... አዕምሮና ልብህ ይስማሙልሃል?... በምትሰማው ወሬ፣ በምታየው ተግባር፣ በምትኖረው ኑሮ ደስተኛ ነህ?...
በጭራሽ!... የአኗኗራችንን ሙሉ ጤነኛነት justify የሚያደርግ አንድም ምክንያት የለም...
[የሆነ ነገራችንንማ አሞናል...]
___
እዚህች ጋ አንዳንድ ጉዳዮች እናንሳና የተፈጥሮን ቅኝት ዓለሚቱ function በምታደርግበት መነጽር እንመልከት...
__
@bridgethoughts
Title: Natural mystic
Singer: Bob Marley
__
@bridgethoughts
.
.
.
የተናገራት ነገር ከንክኗታል... ደጋግማ ሰውነቷን ትመለከታለች... የሰውየው አስተያየት ምቾት አልሰጣትም...
ከጓደኛዬ ጋር ካፌ ውስጥ ተቀምጠን ነበር...
ከውጭ የተቀመጠ አንድ ደንበኛ ልጅቱን የሆነ ነገር ተናግሯት ስትረበሽ አየን... ቃል በቃል ከእርሱ አፍ ባንሰማም ከሰሞኑ በገጠማት ሚጢጢ ህመም ምክንያት ለአመል ያህል 'የቀነሰ' ሰውነቷ ላይ መዘባበቱ ግን ገብቶናል ...
ነገሩ ተፈጥሮአዊ ቢሆንም ሰውየው እንዲህ ሊረዳው የፈለገ አይመስልም... ጭራሽ በወጣች በገባች ቁጥር ሊያሳቅቃት ይሞክር ነበር...
[ህመሙ ከፈጠረባት ድካም በላይ የሰውየው ንግግር ሸክም ሲሆንባት ተሰማን...]
ልጅቱ እኮ በጣም ቆንጆ ናት!!
እርሱ ግን ይሄ አልታየውም... ወይም ደግሞ በእርሱ ቤት ጨዋታ ማሳመሩ ነው...
ልጅቱ እኮ እጅግ ትሁት ናት!!
እርሱ ግን ይሄ አልታየውም... ወይም ደግሞ ያዘነላት መስሎ አንጀት መብላቱ ነው...
ልጅቱ እኮ ዛሬም እንዳማረባት ነው!!
ሰውየው ግን ይህ ግድ አልሰጠውም... ወይም ደግሞ ለሰው ስሜት ፍጹም ደንታ ቢስ ነው...
እናም ማሳቀቅ ብቻ ነው የቻለበት...
___
Unfortunately ለሴት ልጅ የውበትና የማማር ጉዳይ 'አሳሳቢ' ርዕስ ነው... እንደ ወንድ ልጅ Careless ልትሆን የማትፈቅድበት ጉዳይዋ እንደሆነም ይታወቃል...
እናም...
'ዛሬ እንዴት እንዳማረብሽ!' ተብሎ ጨዋታ ይጀመራል... 'ትህትናሽ እኮ የትም አይገኝም' ተብሎ በውዳሴ ይለኮሳል... 'ልብሱን እኮ አሳመርሽው' ማለትም የአባት ነው...
ስለምን...
['ቁንጅና ታጥቦ ባይጠጣም' - ሰውን ስለ ገጹ ውበት አውስቶ ማጉላት ስለ ክሳቱ አውርቶ ከማድማት ይሻላልና]
[አልባስ ከከፈንነት ባይዘልም - ሰውን በልብሱ አመካኝቶ ማድነቅ ገላህ ሳሳ ብሎ ከማድቀቅ ይሻላልና]
ግና እርሱ...
"ከስተሻል" ነው ያላት... [በትክክል ያላትን እዚህ መድገም ነውር ሆኖብኝ ነው]
እናም እርሷ...
በጣም ደበራት!!...
[ሕመሟን ተኝቶ ማዳመጥ ትታ ነው ስራ የገባችው... ከአልጋ ሰው መርጣ ነው በዚህ የተገኘችው... ግና ያልጠበቀችው ሆነና ከፋት...]
___
ነገሩ ተራ አጋጣሚ ሊመስል ይችላል... ስለተለመደም ትኩረት ባይስብ አይገርምም... [በዚህ እግረ መንገድ ግን ልምምዳችን መነቀፍ ይኖርበታል...]
ምን መሰለህ?...
ስንገናኝ ቀልባችን የሚወሰደው በተራ ነገሮቻችን የመሆኑ ጉዳይ የሚያስቆዝም ነው... በአላፊ ጠፊው ላይ እናተኩራለን... በከንቱ ጉዳዮቻችን ላይ እንመሰጣለን... ያልበላንን እናካለን... የሰውን ቅስም እንሰብራለን...
ግልጽ እኮ ነው... "ስጋ ባዳ ነው"... ይመጣል ይሄዳል... ስለወፈሩ ሙላት፣ ስለከሱም ጉድለት የለም...
ሰው ያደረጉን ቁምነገሮቻችን ያሉት እኮ በማይታየው ነገራችን ውስጥ ነው... ደግነታችን፣ ቅንነታችን፣ ታማኝነታችን፣ ፍቅራችን ውስጥ... እኒህን ማየት አንችልም - መረዳት እንጂ...
___
[አየህ የልጅቱ ህመም ጊዜያዊ ነው... በድካም ስለተፈጠረ የሁለትና ሦስት ቀን ዕረፍት ከነመፈጠሩ ያጠፋዋል...]
የምላስ ወለምታ ግን እረፍት አይረታውም...
ስናሳጥረው...
ሰዎች ጉድለቴ የሚሉትን ነገር ማስታወስ ልክ አይደለም... 'በሰው ቁስል እንጨት የመስደድ' ቅሽምና ከሌለብህ በቀር...
ልትረዳው አልያም ልትቀይርለት በማትችለው ሁኔታ ውስጥ ያለን ሰው ብሶት ማባባስ በጎ አይደለም... በጥላቻ ካልታወርክ በቀር...
በቆዳህ ጥራት፣ በስጋህ ክብደት፣ በሃብትህ ብዛትም ሆነ በወንበርህ ክብደት መመካት ስህተት ነው... 'ሰከንዶች የሸሸጉትን አውቃለሁ' የማለት ድፍረት ካልሆነ በቀር...
___
ሁላችንም ሁሉን ነገር በተመሳሳይ መንገድ አንረዳም... የሸክም ልምዳችን ልዩ ልዩ ነው... አንዳንዶቻችን ስንጥር ያጎብጠናል፣ ሌሎቻችን ግንድ ይሰግድልናል...
እናም ይህን አስታውስ...
የቃል ክብሩ - ሳይቀል መነገሩ!!...
___
@bridgethoughts
.
.
.
አንዳንዴ ግን አስባታለሁ...
ወዳጅነታችን መራራቅ ያደበዘዘው፣ የሌላነትም ያጠየመው ነው... እንዲያም ሆኖ ግን አስባታለሁ... የጋራ ነገ እንደሌለን እርግጠኛ ሆኜም ሁሌ አስታውሳታለሁ...
ከግዙፍ የመርሳት አባዜዬ የተፋቱ ሽርፍራፊ ትዝታዎቿ ድንገት ፊቴ ይደቀናሉ...
አስባታለሁ...
አብራኝ እንደማትሆን እያወቀች ትዝታዎቿን እኔ ዘንድ የተወችበትን ብልሃት ብበሳጭበትም አስታውሳታለሁ...
ሄዶ ላለመረሳት፣ 'ርቆ ላለመፋቅ በአዕምሮዬ የሞጀረቻችው መቆሳቁሶች ብዙ ናቸው!...
ባለፈው ወር...
እዚያ የምታውቁት ካፌ ውስጥ ቁርስ ለመብላት ተቀምጬ እያለ አንዲት መለሎ ሴት ስትገባ አየሁ... ስትር ያለው ቁመናዋ እያባበለኝ በፈራ ተባ መሽኮርመም ውስጥ ሆኜ እያየሁዋት ቆየሁ... ከአጠገቤ አለፈች... አንገቴን ወደኋላ ማዞር ፈልጌ ነበር... እፍረት ጨምድዶኝ ተውኩት...
የሽቶዋ መዓዛ ግን 'ማለፍ ክልክል ነው' እንዳሉት ሁሉ አፍንጫዬ ላይ ተሰንቅሮ ቀረ... እናም አልፋ እንዳላለፈች ገባኝ...
'ይህን ሽቶ የት ነበር የማውቀው?'...
አዎን - መሲ ጋ ነው... በተመረጡ የመገናኛ ቀኖቻችን ሁሉ ይህን ሽቱ ነበር ነስነስ አድርጋ የምትመጣው... ተንኮሏ ግን... ምናል አንድ ዓይነት ሽቱ ብቻ ባትቀባ?... [እንዳልረሳት አይደል?...] አፍንጫዬስ ምን ቢሆን ነው ይህን ሽቱ ነጥሎ ማጥፋት ያቃተው?...
ባለፈው ሳምንት...
ከጓደኛዬ ጋር በታክሲ እየሄድን ወግ እንጠርቃለን... ተመስጬ እያወራሁ ሳለ ከወደ ሬዲዮው የተወነጨፈው ዜማ ቀልቤን ወሰደው...
'አንድ ሰው'... የፍቅረአዲስ እንጉርጉሮ... የሆነ ዓይነት ኃይል ስቱዲዮ ተቀምጦ፣ በ remote control ልሳኔን የዘጋው መሰለኝ... መሲ ይህን ሙዚቃ በጣም ትወደው ነበር...
"... አሃሃሃ አንድ ሰው - አሃሃሃ በየጨዋታው ላይ
አሃሃሃ አንድ ሰው - ባይመጣ ትዝታ
አሃሃሃ አንድ ሰው - አሃሃሃ እቃኘው ነበረ
አሃሃሃ አንድ ሰው - ባቲን ለደስታ..."
የወሬዬ በድንገት መቆም ከፊት ያሉ ተሳፋሪዎችን ሁሉ ሳያስገርም አልቀረም... ጓደኛዬ 'ቀጥል እንጂ' እንደማለት በፊቱ አናገረኝ... በረጅሙ ተንፍሼ 'ቆይ ይሄ ብሔራዊ መዝሙር ይለቅ' አልኩት... ተረድቶኛል...
"... ባለጊዜው መጥቶ - ዋውዬ... ዛሬ ባለቀኑ
ተሸኝቷል ትናንት - ዋውዬ... ቀርቶ ሰቀቀኑ
ከርሞ ሲመጣበት - ዋውዬ... ዘንድሮም ይረሳል
እንዲህ ያልፋል እንጂ - ዋውዬ... ቀን መች ይመለሳል..."
አዎን አይመለስም!... እኔን ያመላልሳል እንጂ... ግን እርሷ ይህን ሙዚቃ ከኔ ጋር እያለች እንዲያ በስሜት የምታንጎራጉረው ለምን ነበር?...
በሃሳብ ከመንጎድ ያናጠበኝ ከፊትለፊታችን ቁጭ ብላ ወሬያችንን በትኩረት ትሰማ የነበረች ወጣት የስልክ ጥሪ ነበር...
"... ወደ ኋላ ሄደሽ - በሃሳብ ከማለም
ቀኑ እንዳይመሽብሽ - ትናንት ዛሬ አይደለም..."
በዚህ ዘመን ይህን ሙዚቃ ከመስማት አልፎ የስልኩ ጥሪ የሚያደርግ ወጣት መኖሩ እያስገረመኝ ከነባር ሃሳቤ ተፋታሁ...
ወሬዋን ስትጨርስ ጠብቄ 'የስልክ ጥሪሽ ያምራል' አልኳት...
"ከአንተ ወሬ አይበልጥም" አለች ፍልቅልቅ እያለች...
መውረጃችን ሲደርስ ጓደኛዬ ፈጠን ብሎ 'ሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ወሬ ካስፈለገሽ በዚህ ቁጥር ደውይ' ብሎ ስልክ ቁጥሬን ሰጣት... የሆነ ሰው ጥንድ ሆኜ ማየት ምኞቱ ነው...
___
ዛሬ ረፋድ...
ስልኬ ለስለስ ብላ አንኳኳች... የእረፍት ቀን ነው ብዬ አልጋዬን ሙጥኝ እንዳልኩ ነበር... ስልኬን አነሳሁ፣ የማላውቀው ቁጥር ነበር...
"ሄሎ..." አልኩ... ከወዲያ በኩል ባለፈው ታክሲ ውስጥ ሆኜ የሰማሁት የስልክ ጥሪ ሙዚቃ ተቀበለኝ... ስለማንነቷ ማብራራት አላስፈለጋትም...
___
የትናንትን ሸክም ሳታራግፍ የዛሬን ሰላም ማጣጣም አትችልም፤ በትናንት ጽልመት የተመሰጡ ዓይኖች የዛሬን ውበት ማየት አይችሉም...
ወደ ነገ የሚጓዝ የትናንትን ጓዝ መጣል አለበት...
___
@bridgethoughts
.
.
.
ነገሩን እንዴት መሰለህ የማየው...
የሆነ ሰው አለ አይደል - ደጋግመህ የምታልፍበት መንገድ ላይ የሚቀመጥ... እናም ባየህ ቁጥር "ይሄ ልጅ ሁልጊዜ በዚህ በኩል ሲያልፍ አየዋለሁ" እያለ የሚገረም... የአንተን በዚያ መመላለስ ያወቀው እኮ እርሱም ሁልጊዜ በዚያ የሚቀመጥ ስለሆነ ነው...
ወይም ደግሞ...
"ምን ያፈጥብኛል?" የምትል እንስት ማፍጠጥህን ሳታይህ በምን አወቀች?... በምንም ልታውቅ አትችልም... [ስለዚህ ጉዳዩ ላይ ተባብራለች...]
ነገሩ 'አንተ በሌለህበት መስታወቱ ምን ያንጸባርቃል?' የሚል እሳቤን ይፈጥራል... መስታወቱ ፊት ከሌለህ መስታወቱ 'የመሰወተውን' ልታውቅ አትችልም ማለት ነው... (የመሰወተው ይባላል እንዴ?...)
ነገሩን ወደ ኑረት እንጎትተው...
የሆነ ብሽቅ ሰው ሰደበህ ወይም 'ስምህን አጠፋ' እንበል... [ስምህን በእርሳስ አትፃፍ ብዬህ አልነበር?...ሃሃሃ]... ራስህን ለመከላከል አልያም 'የክብር' ነገር ሆኖብህ ምላሽ ለመስጠት ወሰንክ...
ዌል፣ ምላሽህን መስታወቱ ፊት እንደመቆም አድርገህ ብታስበው ግጭት የመፈጠር ዕድሉ ሰፊ ነው... ነገሩን አልሰማኸው ወይም ትተኸው ቢሆንስ ኖሮ?... በቃ ሰላም!!...
ሃበሻ ድንቅ ብሂል አለችው... 'መተው ነገሬን ከተተው' የምትል... [በዕለታዊ እንቅስቃሴዬ ሁሉ ምርኩዝ የምትሆነኝ mystical ቃል ናት... እርሷን የረሳሁ ዕለት ነው suffer የማደርገው... የምስራቁን ዓለም ትምህርት በሙሉ በአንድ አቢሲኒያዊ ዘዬ ጠቅልል ብባል 'መተው - ነገሬን ከተተው' ነው የምለው'... እንዴት ዓይነት libration መሰለህ - መተው!!!...]
ምንም ነገር የሚኖረው ስንኖር ነው... [ነገሩን በደንብ አስበው የምር... አሁን በዙሪያህ ያለው ነገር ያላንተ ምንድነው?... ስለኖርክ ብቻ ያለ አይመስልህም?... ይገባኛል 'ባልኖርም መኖሩን አላስቀርም' የሚል ሃሳብ እንደፈተነህ... የረሳኸውን ግን ላስታውስህ... 'መኖር' የኖረው 'ኖረህ' ስላየኸው ነው...] አንድ ጊዜ በመኖር 'ያወቅነውን' ነገር እንደሌለ መቀበል ይቸግረናል...
[እዚህች ጋ ትንሽ ተፈላሰፍ... የምታየውን ነገር አንድ ሚሊየን ሰው እያየው ቢሆን እንኳ ያንተን perspective የሚመስል ላይኖር ይችላል... ወይም ደግሞ ወጋየሁ 'ፍቅር እስከ መቃብርን' እየተረከ የሚሰሙት እልፍ ሰዎች - እልፍ ሰብለወንጌልን ነው በምናባቸው የሚስሉት... (ምናብ ለዘላለም ይኑር!... እነ ETV መጥተው 'ሰብለ ይህች ናት' ሲሉህ ግን የምናብህን ሰብለን እየሰረቁህ እንደሆነ አትርሳ... የጋሽ ሐዲስን መጽሐፍ ስታነብ መቼና የቱን የምትስለው፣ ሰውና መልክዓ-ምድሩን የምትኩለው አንተ ነህ... 'ኢቲቢ' ስታይ ግን የዳይሬክተሩ ሰብለ ናት የምትሰጥህ... ምናብህን ከሚበሉ መስኮቶች ራቅ ወዳጄ)... ይህችን 'ወሽመጥ ሃሳብ' ለጊዜው ዝጋትና ያቺ ሁሉ የምናብ ሰብለ የኖረችው በማን መኖር ነው ብለህ ጠይቅ...]
ምን መሰለህ?... 'በሚቀጥሉት ፭ ሰከንዶች ውስጥ ስለ ዝሆን አታስብ' ብልህ በእርግጠኝነት ከዝሆን ውጭ ማሰብ አትችልም... ጥያቄው ግን - 'ስለ ዝሆን ምንም ዕውቀት ባይኖርህስ?' የሚል ነው... ስለምን ታስባለህ?... አስቀድሞ እውቀቱ በሌለህ ነገር ላይ ብዙም አትቸገርም...
ነገሩን መረር እናድርገው እንግዲህ...
በሰዎች አንዳች ተግባር ስትፈርድ ውስጥህ ያለው ተመሳሳይ የጥፋት ስሜት አጋዥ ሆኖ ይቆማል... ምን ማለቴ መሰለህ?... ሰዎችን የምትኮንንበት ጥፋት በሙሉ አንተም ውስጥ አለ...
ሩሚ እንዲህ ይላል... “The fault you see in your brother is really in you.”
አየህ - 'ከደሙ ንጹህ ነኝ' ዓይነት እጅ ልቅለቃ ብዙ አያዋጣም... ብዙዎቻችን ሌሎች ዓይን ውስጥ ያለ ብናኝ እንከን ሳይቀር ማየት የማያስችለን ምሰሶ ዓይናችን ውስጥ ተጋድሟል...
የ Lao Tzu ቃል ለዚህ ፈውስ ነው... “Knowing others is intelligence. Knowing yourself is wisdom.”
___
ምን እያልኩ ነበር?... [እንጃ... ጠፋብኝ...]
___
[ይህችን ሃሳብ የሰኞ ዋዜማ 'ተብሰልስሎት' በላት... የተጀመረም ያለቀም ነገር የላትም... ሃሳብ ከጫረች በቃት! - ዓላማዋን አሳክታለች...]
___
@bridgethoughts
.
.
.
የሻይ ቡና ቆይታችን ሲጠናቀቅ የነበረኝ ግምት ወደ ቤቷ እንደምሸኛት ነበር...
ያ ግን አልሆነም...
"እኔ 'ምልህ፣ ባለፈው የሩሚን መጽሐፍ ሰጥሻለሁ ብለኸኝ ነበር አይደል?" አለችኝ...
"አዎን"
"ዛሬ እፈልገዋለሁ፣ ልትሰጠኝ ትችላለህ?"...
"እንዴታ... እሰጥሻለሁ እንጂ... ግን አሁን..." የሞባይሌን ሰዓት አየሁት... ከምሽቱ 12:30...
"አሁን ምን?" እንደመከፋት አለች...
"መሽቷል ብዬ ነው... ቤቴ ሩቅ አይደል፣ ስንመለስ ይመሽብሻል"... ቀበጣጠርኩ... ጥያቄዋ ድንገት ትንፋሽ ያሳጣኝ መሰለኝ...
"ግድየለም አንድ ታክሲ አይደል?... እንደርሳለን፣ ደግሞም ብዙ አልመሸም"...
[ጉድ ፈላ!!... ምን አስባ ነው?...]
"ለምን ነገ አላመጣልሽም ማር"... ፊቷን በጥንቃቄ አጠናሁት...
"አይሆንም ዛሬ ነው የምፈልገው!" ፈርጠም አለች...
በአንድ ጊዜ ፍርሃትና ጭንቀት ቅኝ ግዛታቸው አደረጉኝ... የእርሷን በጣሪያዬ ስር መገኘት እንደ ልዩ ስጦታ የምቆጥረው ነገር ቢሆንም ቤት እንሂድ ስላለችኝ ብቻ ፈንጥዤ እንሂድ የማልልበት ምክንያት ነበረኝ...
ውዝግብ ውስጥ እንደገባሁ ሲገባት "ምነው ችግር አለ?" አለችኝ...
"ኧረ ምንም ችግር የለም... ብቻ..."
"ብቻ ምን?... ቤትህ መምጣቴ አያስደስትህም?" ኮስተር ብላ ነበር...
"እንዴት እንደዚያ ታስቢያለሽ?... ያውም አንቺ ፈልገሽ?... በጣም ነው እንጂ የሚያስደስተኝ..."
[ለምንድነው ግን እንዲህ የምታስጨንቀኝ?...]
"የደበቅሃት አለች እንዴ?" ብላ በዓይኗ ሳይቀር ጠየቀችኝ...
"ማሂ!" ጮህኩባት... "ምንድነው የምታወሪው?"...
አብሮ ያለመሄድ ፍላጎት ባሳየሁዋት ቁጥር እንዲህ ዓይነት ግምት እንዳትይዝ ስፈራ ነበር...
___
ሃሳቧን ማስቀየር ስላልቻልኩ ታክሲ ይዘን ወደ ሰፈሬ አመራን... የተኮራረፍን ይመስል አንዳች አልተነፈስንም... ታክሲው ቀስ እንዲል የጀመርኩት ጸሎት ከማረጉ በፊት መንገዱ አለቀ...
"ወራጅ አለ" አልኩ... ረዳቱ ታክሲውን ደብድቦ አስቆመው... ወረድን... ጭንቀቴ ግን እኔን ታክሲ አድርጎ ጉዞውን ቀጥሏል...
እየመራሁ የኪራይ ቤቴ አደረስኳት... እንደተዘጋጋን... ሆኖም በሩን ለመክፈት አቅም አጣሁ... [እጄ እንደ መንቀጥቀጥ አለብኝ]
"እኔ ልክፈትልህ እንዴ?" አሾፈችብኝ...
ወደ ውስጥ ገባን...
'ያንተ ያለህ!'... የፈራሁት ይህን ነበር...
ቤታችንን ውስጥ ሌላ ሰው ሲገኝ ብቻ የሚፈጠር ትርምስ አለ ልበል?... በአዘቦቱ ምንም የማይረብሸኝ ቤት ፍቅረኛዬን ይዤበት ስገባ አህያ የወለደበት መስሎ ጠበቀኝ...
[ሳይታጠቡ አንድ ስርቻ ውስጥ የታጎሩ፣ ቢወረወሩ ግንባር ለመፈንከት አቅም የማያጡ ካልሲዎች... ባዶ የወተትና እርጎ ማሸጊያ ፕላስቲኮች፣ መወልወያ የናፈቀው ወለል፣ ከአልጋ እስከ ምንጣፍ የተዘረጋ የልብስ ኤግዚቢሽን... የፌስታል መዓት... የሻማ ቁራጭ፣ የክብሪት እንጨት፣ ብዙ የሃይላንድ ዕቃ፣ በአቧራ የተሸፈነ የመጽሐፍ መደርደሪያ፣ ድር የጎበኘው ግርግዳ... የታፈነ አየር... ምኑ ቅጡ...]
'እንዴት እስከዛሬ አላስተዋልኩትም?'
ትዝ ሲለኝ ቁጭ በይ እንኳ አላልኳትም... የቤቴን ሁኔታ በዓይኖቿ ስታበጥር ነበር... አንድ ወንበር ስቤ በሶፍት ለማጽዳት ስሞክር "ተወው ተወው አልቀመጥም፣ ይልቅ ሸኘኝ..." አለችኝ... በጣም ደነገጥሁ...
"እንዴ፣ ማሂ! በቃ?... ለዚህ ነው የመጣሽው?" ግራ ተጋባሁ...
"የምፈልገውን አግኝቻለሁ፣ ይልቅ መሽቷል እንሂድ" ፊቷን አዙራ ወደ በሩ አመራች... መጽሐፉን እንኳ አልጠየቀችኝም...
"ማሂዬ፣ ይቅርታ፣ ቤቴ ደብሮሽ ነው አይደል? በእናትሽ አትቀየሚኝ፣ ቤቴ ሰው ይመጣል ብዬ ስላላሰብኩ ነው ቸል ያልኩት፣ ላስተካክለው እችላለሁ..." መረጋጋት ተቸገርኩ...
"የመጣሁት መጽሐፍ ፈልጌ አይደለም፣ ሰው አይመጣበትም የምትለውን ቤትህን እንዴት እንደምትይዘው ማየት ፈልጌ እንጂ..."
"አልገባኝም..." ብስጭት ውስጥ እየገባሁ ነበር...
"አየህ... አንተ ማለት 'ማንም አያየኝም' ስትል የምታደርገውን ነህ... መምጣቴን አውቀህ ብትሰተር በእኔ ፊት ለማስመሰል እንጂ የሆንከውን ለመኖር ነው ልል አልችልም ነበር... ድንገት መምጣት ያስፈለገኝ ለዚህ ነው..."
ዝም አልኩ... ጸጥ ረጭ!!... ቤቴም ተባበረችኝ... ውጪውም አገዘኝ... በዚህ ሁኔታ ዝም ያልኩበትን ሁኔታ በጭራሽ አላስታውስም... እፍረት ጨመደደኝ...
"እንሂድ?" አለችኝ ደግማ፣ ደረጃውን እየወረደች...
ልሸኛት ወጣሁ... ታክሲ ተራ እስክንደርስ ምንም አላወራንም...
"ሁለት ሰው?" አለ ረዳቱ እንዳየን...
"አንድ ብቻ!..." ፈጥና መለሰችና ነጠለችኝ... ለነገሩ ታክሲውም ያለው የአንድ ሰው ቦታ ነበር...
ከመግባቷ በፊት እንደተለመደው አቅፋ እንድታሰናብተኝ፣ እንደምወደው አንገቷን እንድስማት ጓጉቼ ነበር...
አልሆነም...
ቻው እንኳ ሳትለኝ ዘው ብላ ገባች...
ታክሲው ይዟት ተፈተለከ... ባለሁበት ደርቄ ቀረሁ...
___
አንድ ፈተና ብቻ ሰጥታኝ ከ 100 አረመችው... እርሱንም ወደቅሁ...
"ሰዎች ለእኔ ያላቸውን ፍቅር የምመዝነው ለራሳቸው ባላቸው ክብር ውስጥ ነው" ብላኝ ነበር...
___
@bridgethoughts
ለጥንቃቄ...
___
የማይጠየቁ ጥያቄዎች...
__
1. ሰላማዊ እንቅልፍ ተኝተህ ስምህን አስር ጊዜ ጠርቶ ቀስቅሶህ ልክ ስትነቃ "ውይ! ተኝተሀል እንዴ?" የሚል ሰው አያበግንህም? ባልተኛ ነው የቀሰቀስከኝ ታድያ?...
___
2. "የማትፈልገው እንትን አለህ?" (ሲጀመር የማልፈልገው ነገር አይኖረኝም! ከኖረኝ በኋላ እንደማልፈልገው ካወቅሁም እስካሁን እጥለው ነበር)
___
3. ሻወር ቤት ገብተህ አንዱ ያንኳኳና "Friend ጨርሰሻል?" ይልሃል... (ከጨረስኩ ምን እሰራለሁ?)
___
4. በር ሳንኳኳ ከውስጥ "ማነው?" እያለ ሊከፍት የሚመጣ ሰው ይገርመኛል! ሌባ ብሆን "ሌባ ነኝ!" እንድለው ነው? መክፈቱ ካልቀረ ማንስ ብሆን ምን ይጠቅመዋል? "መጣሁ!" ማለት አይሻልም?...
___
5. "አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?" ብለህ አትጠይቅ! 'አንድ' ካልክ እኮ በቃ "አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?" ስትል ጥያቄህን ጨረስክ...
___
6. ቂቅ ብለህ ዘንጠህ መጥተህ "አምሮብኛል አይደል?" ብለህ ከነ መልሱ አትጠይቀኝ... "አምሮብኛል?" የሚለው ጥያቄ ብቻ ይበቃል አይደልን ከጨመርክ እኮ ሼም ይዞኝ "አዎ" እንድል እያስገደድከኝ ነው... ወይም ደግሞ እንዳማረብህ አውቀሀል ማለት ነው... ታዲያ ለምን ታደርቀኛለህ?...
___
7. እርቦኝ፣ ጠምቶኝ፣ ደክሞኝ ልክ ቤት ስገባ 'መጣህ?' አትበሉኝ.. እንግዲህ እኔ እስከማውቀው ድረስ ስለመጣሁ ነው የታየኋችሁ! ይልቅ የሚበላ የሚጠጣውን አቅርባችሁ ፈውሱኝ...
___
8."ሰዓት ስንት ነው?" ስልህ "አሁን?" አትበለኝ... ታዲያ መቼ ሊሆን ይችላል? ወይስ አቆጣጠሩን ስለማታውቅበት ጊዜ ለመፍጀት ነው?
___
9. 'Password'ህን ንገረኝ? አይባልም... ከነገርኩህማ ምኑን password ሆነው ታዲያ?
___
10. 'ምን ልጋብዝህ?' አይባልም... ግብዣ በጋባዥ እንጂ በተጋባዥ ውሳኔ አይካሄድም... ሼም ይዞኝ የወረደ ነገር እንዳዝ ፈልገህ ካልሆነ በስተቀር!
___
11. ለቅሶ ቤት ሄደህ የአሟሟቱን detail አትጠይቅ! ማስተዛዘን እኮ ሃዘን ማረሳሳት እንጂ ማባባስ አይደለም...
___
[ይህ ጽሑፍ የድልድይ አይደለም፤ ቆየት ባለ ጊዜ ከፌስቡክ ገጽ የተወሰደ ነው...]
___
@bridgethoughts